1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሩሲያ የዩክሬን እህል ሽያጭ ስምምነትን ማፍረስዋ

ሰኞ፣ ጥቅምት 21 2015

ሩሲያ በመንግሥታቱ ድርጅትና ቱርክ ሸምጋይነት በጥቁር ባሕር ወደቦች ተከማችቶ የሚገኘው የዩክሬን እህል ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ የደረሰችበትን ስምምነት ያቋረጠች መሆኑን ትናንት እሑድ አስታውቃለች። ይሁንና እህል የጫኑ በርካታ የዩክሬይን መርከቦች እህል ጭነዉ ከዩክሬይን የጥቁር ባህር ተነስተዋል።

https://p.dw.com/p/4Itr5
BdTD | Türkei
ምስል Yasin Akgul/AFP

ሩሲያ ያገደችው የዩክሬን እህል ሽያጭ

ሩሲያ በመንግሥታቱ ድርጅትና ቱርክ ሸምጋይነት በጥቁር ባሕር ወደቦች ተከማችቶ የሚገኘው የዩክሬን እህል ለዓለም ገበያ እንዲቀርብ የደረሰችበትን ስምምነት ያቋረጠች መሆኑን ትናንት እሑድ አስታውቃለች።  ስምምነቱ ከሐምሌ ወር ወዲህ  ብቻ ዩክሬን  ዘጠኝ ሚሊዮን ቶን ስንዴና የቅባት እህሎችን  በ397 መርከቦች ለዓለም ገበያ እንድታቀርብ ያስቻለ ሲሆን፤ ሩሲያም ማዳበሪያና እህል ለውጭ ገበያ እንድትልክ የረዳ ነበር። ይህም የተፈጠረውን የእህል እጥረት በመቅረፍ የዓለምን የእህል ዋጋ በ15 ከመቶ ቀንሶት ነበር ተብሏል። አሁን ግን ሞስኮ በተሰነዘረባት ወታደራዊና የድሮን ጥቃት ከስምምነቱ ለመውጣት የተገደደች መሆኑን ገልጻለች። የሩሲያ መከላካይ ሚኒስተር ትናንት ባወጣው መግለጫ ባለፈው ቅዳሜ ብቻ በክሬሚያ ሴቭስቶፖል አቅራቢያ በነበረው የባሕር ኃይል መርከቧ ላይ 16 የድሮን ጥቃቶች እንደተሰነዘሩበትና ይህም በተለይ በብሪታኒያ የባሕር ኃይል ርዳታ ወይም ስልጠና የተፈጸመ እንደሆነ በመግለጽ ከስምምነቱ ለመውጣት የተገደደችበትን ምክኒያት አስታውቋል።  
 ዩክሬንም ሆነች ብሪታኒያ ግን የሞስኮን ክስ መሰረተ ቢስና የተለመደ በማለት ነው ያስተባበሉት። ፕሬዝዳንት ቮሊድሜር ዜለንስኪ እርምጃውን የሩሲያ እህልን የጦር መሳሪያ የማድረግ እቅድ አካል እንደሆነ ነው የገለጹት፤ «ውሳኔው ሩሲያ በአፍሪቃና እስያ ረሀብ እንዲከሰት ያላትን ፍላጎት በግልጽ የሚያሳይ ነው» በማለት ዓለም ሁሉ ሩሲያን  እንዲያወግዛት ጥሪ አቅርበዋል። 
አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የመንግሥታቱ ድርጅትና ኔቶም፤ ሩሲያን በዚህ እርምጃዋ አጥብቀው አውግዘዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሞስኮን እርምጃ ትልቅ አሻጥር፤ በማለት ነው የኮነኑት። «በጣም የሚያበሳጭ ነው፤ ረሀብን የሚጨምርና የሚያስፋፋ እርምጃ፤ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ምንም ምክኒያት የለም» በማለት ፕሬዝዳንት ፑቲን ውሳኔውን እንደገና እንዲያዩት ጠይቀዋል። የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ቦርየልም በቲውተር ገጻቸው «ሩሲያ በጥቁር ባህር ስምምነት ያላትን ተሳትፎ ለማቋረጥ መወሰኗ በዓለም ላይ የተፈጠረውን የምግብ እህል እጥረት ሊያባብሰው ይችላል» በማለት ውሳኔዋን እንደገና እንድታጤን አሳስበዋል። ሁሉም የአውሮጳ ህብረትና የኔቶ አገሮች በተመሳሳይ ስሜት የሩሲያን እርምጃ እንዳወገዙ ነው የተሰማው።  
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴረሽም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመግለጽ በችግሩ ላይ ለመወያየትና መፍትሄ ለማፈላለግ ለዛሬ የነበራቸውን ሌላ የሥራ ጉብኝት ሰርዘው ከባለድራሻ አካላት ጋር  እየተወያዩ  እንደሆነ አስታውቀዋል። የቱርክ ባለሥልጣኖችም ከሩሲያ አቻዎቻቸው ጋር በመወያየት ሩሲያ ስምምነቱን እንድታከብር ለማግባባት እየሞከሩ ነው ተብሏል። ባለፈው የሐምሌ ወር የተፈረመው ይህ  ዩክሬን በጥቁር ባሕር ወደቦች እህል ወደ ውጭ እንድትልክ የሚፈቅደው ስምምነት፤  በኅዳር ወር አጋማሽ እንዲታደስ የሚጠበቅ ነበር። ሩሲያ ግን ስምምነቱን ትናንት አፍርሻለሁ ከማለቷ በፊትም በዓላማና ትግበራው ላይ ቅሬታ እንዳላት ስትገልጽ ቆታለች።

Irland | Ankunft eines Getreide-Frachtschiff aus der Ukraine
ምስል Clodagh Kilcoyne/REUTERS
Türkei, Istanbul | SSI Invincible II
ምስል Francisco Seco/AP/picture alliance

የስምምነቱ ዋና አላማ የዩክሪንና የሩሲያም የእህል ምርት ያለምንም ችግር ተጓጉዞና ለገበያ ቀርቦ በደቡብ ባሉ አገሮች በተለይም በአፍሪቃ ሊደርስ የሚችለውን የእህል እጥረትና የረሀብ አደጋ ለማስቀረት ቢሆንም፤ እስካሁን ግን ለነዚህ አካባቢዎች የደረሰው የእህል መጠን ከተላከው 3 ከመቶ ብቻ እንደሆነና ሌላው በአውሮጳ እንደቀረ በመግለጽ አውሮጳውያኑን በአስመሳይነት ስትከስ ቆይታለች። ይህ ሁኔታ ተሻሽሎና ስምምነቱ ተራዝሞ ከዩክሬንም ሆነ ሩሲያ ለዓለም ገበያ የሚቀርበው የእህል ምርት የበለጠ ይሳለጣል ተብሎ ሲጠበቅ፤ ይህ ውሳኔ መወሰኑ ችግሩን እንዳያባብሰው አስግቷል። ዩክሬን በስንዴና የቅባት እህሎች ምርት የምትታወቅ ሲሆን በሐምሌ ወር ስምምነት በተደረሰበት ወቅት ለውጭ ገበያ የተዘጋጀ 20 ሚሊዮን ቶን በመጋዝኗ እንደሚገኝ ተገልጾ ነበር። አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ዩክሬን የእህል ምርቷን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችላትን የባሕርና የየብስ አማራጭ መስመሮችን እንደሚያፈላልጉ እየገለጹ ቢሆንም፤ ይህ ግን አስቸጋሪና ውስንም እንደሚሆን ነው የሚነገረው። የጦርነቱ እሳት በርዶና የአገሮቹ ዲፕሎማሲያዊ ጦርነት ረግቦ የዩክሬንም ሆነ የሩሲያ የስንዴ ምርት ለገበያ መቅረብ ካልቻለ፤ በተለይ በአፍሪካና ደቡብ አሜርካ ጭምር የምግብ እህል እጥረት ሊፈጠርና የረሀብ አደጋም ሊኖር እንደሚችል ስጋትቸውን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው።  

ገበያው ንጉሤ 
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ