ሠሚ ያጣው የዛይሴዎች አቤቱታ
ረቡዕ፣ ሰኔ 19 2016ሠሚ ያጣው የዛይሴዎች አቤቱታ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ በሚገኙ የዛይሴ ማህበረሰብ አባላት ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የዘፈቀደ እሥርና ወከባ እየተፈጸመ ይገኛል ሲሉ ነዋሪዎችና የህዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባላት ገለፁ ፡፡ የዞኑና የወረዳው የፀጥታ አባላት ሰሞኑን በሌሊት ቤት ለቤት በመዘዋወር ወጣቶች ፣ ሴቶች እና ቄሳውስቶችን ጨምሮ 112 የማህበረሰቡ አባላትን ይዘው ማሠራቸውን ነው ነዋሪዎቹና የእንደራሴ ምክር ቤቱ አባላቱ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት የዘፈቀደ እሥርና ወከባው እየተፈጸመ የሚገኘው በወረዳው ዛይሴ ደንብሌ ፣ ዛይሴ ኤልጎ እና ዛይሴ ወዘቃ በተባሉ የገጠር ቀበሌያት ውስጥ ነው ፡፡
የአቶ ጥሩነህ ስደት
በጋሞ ዞን አርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የዛይሴ ደንብሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶአደር ጥሩነህ አዲስ በሥጋት መንደራቸውን ከለቀቁ ከሁለት ሳምንታት በላይ ማስቆጠራቸውን ይናገራሉ ፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የጋሞ ዞን እና የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የፀጥታ አባላት ቤት ለቤት በሚያደርጉት አሰሳ የተነሳ መሆኑን የጠቀሱት ጥሩነህ “ አሁን ወደ ሌላ ሥፍራ ተሰድጄ ነው ያለሁት ፡፡ ያም ሆኖ አጎቴ ፣ የአጎቴ ሚስት እና ልጄን ጨምሮ አብዛኞቹ የቤተሰብ አባሎቼ ታስረው ተወስደውብኛል “ ብለዋል ፡፡በግጭት ሥጋት ውስጥ የሚገኙት የአርባ ምንጭ ዙሪያ ቀበሌያት
አቶ አብረሃም ኦላሼ በጋሞ ዞን የዛይሴ የምርጫ ክልልን በመወከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴ መሆናቸውን ይናገራሉ ፡፡ አቶ አብረሃም በአካባቢው እሥርና ወከባው እየበረታ የመጣው ከሁለት ሳምንታት በፊት የማህበረሰቡን የአዲስ ዓመት በዓል ለማክበር የተሰባሰቡ ወጣቶች ከፀጥታ አባላት ጋር ተጋጭተው አምስት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው ይላሉ ፡፡ የፀጥታ አባላቱ እስከ ትናንት ድረስ ቤት ለቤት በመዘዋወር ፈጸሙት ባሉት እሥር ወጣቶች ፣ ሴቶች እና ቄሳውስቶችን ጨምሮ 112 ሰዎች ተይዘው መወሰዳቸውን ገልጸዋል ፡፡
የእሥሩ ዳራ
የዛይሴ ደንብሌ ነዋሪው ጥሩነህ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴው አቶ አብረሃም ለእሥርና ወከባው የአዲስ ዓመት በዓል ለማክበር የተሰባሰቡ ወጣቶች መነሻ ቢደረጉም ዋናው ምክንያት ግን ሌላ ነው ይላሉ ፡፡ የዘይሴ ህዝብ ከቅርብ ጊዜ ዓመታት ወዲህ እያነሳ የሚገኘው የራስ አስተዳደር ጥያቄ መኖሩን የጠቀሱት ጥሩነህ እና አብረሃም “ ይህ በልዩ ወረዳ የመደራጀት ጥያቄ በጋሞ ዞን እና በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ፖለቲከኞች ዘንድ አልተወደደም ፡፡ የእሥርና ወከባው ዓላማም በማህበረሰቡ ዘንድ ፍርሃትን በመፍጠር የመደራጀት ጥያቄው እንዳይነሳ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ የሚገኝ ነው “ ብለዋል ፡፡አሳሳቢው የሰብአዊ መብት ጥሰት በጋሞ ዞን
የዋና አስተዳዳሪው ቅድመ ሁኔታ
ነዋሪዎቹ ባነሱት ቅሬታ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቃፌ ቃፊሬ “ እከሌ እንደዚህ ታሠረ እከሌ እንደዚህ ሆነ ብዬ የምሰጠው ምላሽ የለም “ ብለዋል ፡፡ ምላሽ መስጠት ያልፈለጉበትን ምክንያት አሁንም በዶቼ ቬለ የተጠየቁት ዋና አስተዳዳሪው “ ለእኛ ያልቀረበ ጥያቄ እናንተ [ ዶቼ ቬለ ] ጋር ሲመጣ መቀበል አልነበረባችሁም ፡፡ አሁን እኔ መረጃውን የምሰጠው ቅሬታ አቅራቢዎቹ መጀመሪያ እኔ ጋር ቀርበው ካመለከቱ በኋላ ነው “ በሚል ቅድመ ሁኔታ የሚመስል ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡
ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምላሽ ለማግኘት ለጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ ቢደውልም ስብሰባ ላይ በመሆናቸው ማናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል ፡፡ ዋና አስተዳዳሪው በእጅ ሥልካቸው አጭር የጹሁፍ መልዕክት ቢላክላቸውም መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ