1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ምን አለ ልጆቻችንን ብናሳድግበት…?" የሾፌሮች ተማጽኖ

ረቡዕ፣ መጋቢት 14 2014

የኢትዮጵያ ገበያ የሚያሻውን ሸቀጥ፣ ማምረቻዎች የሚፈልጓቸውን ግብዓቶች፣ የገቢ እና ወጪ ንግድ ዕቃዎች በሚያጓጉዙ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዘርፉን ሥጋት ውስጥ ጥለውታል። የከባድ መኪና ባለቤቶች፣ ማኅበራት እና አሽከርካሪዎች ሥራቸው በአንጻራዊነት የጸጥታ ችግር በማይበረታባቸው አካባቢዎች ብቻ ወደ መገደብ ማዘንበል ጀምረዋል

https://p.dw.com/p/48wNx
Dschibuti Hafen
ምስል DW/J. Jeffrey

ከኤኮኖሚው ዓለም፦የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ የተሸከመው የማጓጓዣ ዘርፍ ፈተናዎች

ከጅቡቲ ኮንቴነር የጫነ ከባድ መኪና እያሽከረከሩ ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ የሚያዘግሙት ሾፌር በተበላሸው መንገድ በሰዓት አንድ ኪሎ ሜትር ገደማ እየነዱ ኢትዮጵያ ድንበር ለመድረስ ይጓዛሉ። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት አሽከርካሪ በጅቡቲ ግዛት መኪናቸውን አቁመው ለዶይቼ ቬለ ስለጉዟቸው በሰጡት ማብራሪያ "ከዚህ ኢትዮጵያ ድንበር 85 ኪሎ ሜትር ነው። ቢያንስ 65 ኪሎ ሜትሩ ወደ አንድ ቀን ይፈጃል" ሲሉ ተናግረዋል።

"በጣም የተሻለ ነጻነት ያለው፤ በሰላም የምንሔድበት" የሚሉት እና በጅቡቲ ግዛት ያለው መንገድ የጉዟቸውን ፍጥነት አዝጋሚ ቢያደርገውም ለሕይወታቸው የሚያሰጋ ጥቃትን አይፈሩም። "እንቅልፍህ ከመጣ የትም ቦታ ላይ አቁመህ መተኛት ትችላለህ"ሲሉ ይናገራሉ።

የጅቡቲን ግዛት ጨርሰው የኢትዮጵያን ድንበር ሲሻገሩ የመንገዱ ሁናቴ ቢስተካከልም የጸጥታ ሥጋት ይፈጠራል። "ከጋላፊ እስከ ሚሌ ያለው ነገር በአንጻራዊነት ሰላም ነው። ከሚሌ በኋላ ከቀን ስስድስት ሰዓት በኋላ ለማሽከርከር ሞራል የለንም" የሚሉት አሽከርካሪ ጉዟቸውን በሚቀጥለው ቀን ማለዳ ከሌሎች ባለደረቦቻቸው ጋር ይጀምራሉ።

"የሚያስፈራውን  ቦታ ለማለፍ ሳናርፍ ነው የምንነዳው። ለምሳሌ ከሚሌ አዲስ አበባ ርቀቱ 518 ኪሎ ሜትር ነው። በዚያ ውስጥ እስከ አዋሽ በጣም በሥጋት ነው የምንነዳው። ለምግብ እንኳ የምንቆመው ገዋኔ በሚባለው ከተማ ነው። ከዚያ በመሐል አንቆምም" ሲሉ የመንገዳቸውን ሁኔታ አስረድተዋል።

Dschibuti Containerhafen und Rotes Meer
የጅቡቲ ወደብ የኢትዮጵያን 98.6 በመቶ የገቢ እና ወጪ ሸቀጥ ያስተናግዳል።ምስል Getty Images/AFP/S. Maina

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ውጥንቅጥ እና የጸጥታ መጓደል ዳፋ

ይኸ ጥንቃቄ በመንገድ ላይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ለመሸሽ የሚደረግ ጥረት ነው። ይኸ ሙከራ ግን ሁልጊዜ አይሳካም። ባለፉት የተወሰኑ አመታት ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ ከሚያመራው ዋና አውራ ጎዳና በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የአሽከርካሪዎችን ሕይወት የነጠቁ በርካታ አደጋዎች እና ጥቃቶች ተፈጽመዋል። የአገሪቱ የፖለቲካ ምስልቅልቅል እና ያስከተለው የጸጥታ መጓደል ለዚህ ከፍ ያለ ሚና አበርክቷል።

ጣና የባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤትን ጨምሮ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በጻፈው አቤቱታ "ግድያ እና አፈናን" ጨምሮ በሾፌሮች ላይ እየተፈጸሙ ነው ያላቸው በደሎች መፍትሔ እንዲፈለግላቸው ባለፈው የካቲት አጋማሽ ጠይቆ ነበር።

ማኅበሩ እንደሚለው በአፋር ክልል ከሚሌ እስከ አዋሽ አርባ፤ በኦሮሚያ ክልል ከፍቼ ጎሀ ጽዮን እስከ አባይ ድልድይ ባለው መንገድ አሽከርካሪዎች "ከፍተኛ በደል እየተፈጸመባቸው ይገኛል።" በአማራ ክልል ጎንደር፣ አብርሃ ጅራ፣ ዳንሻ ከጎንደር ሸኸዲ፤ ከጋይንት ደብረ ታቦር ገረገራ ያሉ ቦታዎች ተመሳሳይ የጸጥታ ችግር ያለባቸው እና ለአሽከርካሪዎች ፈታኝ የሆኑ ናቸው። በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ወደ ታላቁ የኅዳሴ ግድብ የሚያመራው መንገድ እና የወለጋ መስመር ትኩረት የሚያሻቸው እንደሆኑ በማኅበሩ ተጠቅሷል።

"ከጸጥታው አንጻር በጣም ከባድ የሚባል ፈተና እየደረሰብን እንኳን በዚያ ውስጥ እያለፍን ነው የምንሰራው" የሚሉት የሰብሪና ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ማጓጓዣ ማሕበር ኃላፊ ወይዘሮ ኑረያ በድሩ ዘርፉ ለአንድ እና ሁለት ቀናት እንኳ ቢቆም "በጣም ከባድ የሆነ ቀውስ ውስጥ ነው የምንገባው" የሚል ሥጋት አላቸው።  

"አንድ አሽከርካሪ ሕይወቱን መስዋዕት እያደረገ ነው ሲሰራ የነበረው። አንድም ራሱን ለመመገብ ነው፤ ሁለትም የአገሪቷን ኤኮኖሚ ለማገዝ ነው። ግድ ስለሆነበት ነው የሚሰራው። አንዳንዴ አሽከርካሪው መኪናውን አቁሞ የሚጠፋበት ጊዜ አለ። የራሱም ሕይወት አደጋ ውስጥ የሚወድቅበት አጋጣሚ አለ" እያሉ ወይዘሮ ኑረያ ፈተናውን ይዘረዝሩታል።

Äthiopien Addis Ababa - Neuer Zug verbindet Hafen und Stadtzentrum
ኢትዮጵያ ከውጪ አገራት የምትገዛውን እና ለዓለም ገበያ የምታቀርበውን ሸቀጥ በባቡር ትራንስፖርት ብታመላልስም የደረቅ እና ፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ከባድ መኮኖች አሁንም ሚናቸው ከፍ ያለ ነው።ምስል picture-alliance/Photoshot/Xinhua/S. Ruibo

ኮንቴነር ጭነው ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ የሚያዘግሙት ሾፌር ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ፣ ሐዋሳ እና ድሬዳዋ ከሚያመሩት መንገዶች ውጪ ለሥራ መንቀሳቀስ ፈጽሞ አይፈልጉም።  ውሳኔያቸው የሥራው ጠባይ በሚያስከትለው እስከ ሞት ከሚደርስ የአደጋ ሥጋት የመነጨ ነው። አሽከርካሪው በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ የተሰማራ ጓደኛቸው የገባበት ከጠፋ ሰነባብቷል። ድምጹ የራቀ ጓደኛቸው በሚያሽከረክረው ከባድ መኪና የጫነውን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ አራግፎ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ላይ ሳለ በታጣቂዎች እጅ መውደቁን እንደሰሙ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

"አስቆሙት፤ መኪናውን አቃጠሉት እሱን ይዘውት ሔዱ። ከዚያ በኋላ በስልኩ ሲደወል ገንዘብ አምጡ አሉ። ሞቷል ወይም አለ አይሉም። መኪናው ግን ተቃጥሏል" የሚሉት አሽከርካሪ ባለፉት ቀናት በቅርቡ ለተገላገለች ድምጹ የጠፋ ወዳጃቸው ባለቤት እርዳታ እየተሰበሰበ እንደነበር ተናግረዋል።

"ምን አለ ልጆቻችንን ብናሳድግበት?" የሹፌሮች ተማጽኖ

እንዲህ አይነቶቹ ጥቃቶች እና የጸጥታ መጓደል ያስከተለው ዳፋ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግድ የሚጋባ ነው። የደረቅ እና ፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ከባድ መኪና ባለቤቶች፣ ማኅበራት እና አሽከርካሪዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሥራቸው በአንጻራዊነት የጸጥታ ችግር በማይበረታባቸው አካባቢዎች ብቻ እንዲወሰን ይሻሉ።   

Karte Äthiopien Ethnien EN
ባለፉት የተወሰኑ አመታት ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ ከሚያመራው ዋና አውራ ጎዳና በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የአሽከርካሪዎችን ሕይወት የነጠቁ በርካታ አደጋዎች እና ጥቃቶች ተፈጽመዋል። የአገሪቱ የፖለቲካ ምስልቅልቅል እና ያስከተለው የጸጥታ መጓደል ለዚህ ከፍ ያለ ሚና አበርክቷል።

በገቢ እና ወጪ ንግድ ላይ በተሰማራ የኢትዮጵያ ኩባንያ የሎጂስቲክስ ሱፐርቫይዘር ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙት አቶ ረጋሳ አበበ በሾፌሮች ላይ የሚፈጸም ጥቃት እና በጸጥታ ምክንያት ዘርፉ የገባበት ችግር ያስከተለው ዳፋ በሥራቸው ላይ ጫና ማሳደር ጀምሯል። ኩባንያቸው ወደ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ቡና፣ የቅባት እህሎች እና የድንጋይ ከሰል የመሳሰሉ ሸቀጦችን ከክልሎች ለማጓጓዝ የሚያደርገው ጥረት በዚሁ የጸጥታ መጓደል ሳቢያ ችግር ይገጥመዋል።

ዕቃ ለመጫን ካመሩባቸው አካባቢዎች ተመልሰው እንዳይወጡ ከባድ መኪኖች ጭምር የተከለከሉ መኖራቸውን ለዶይቼ ቬለ ያስረዱት አቶ ረጋሳ ይኸ አሽከርካሪዎች የጸጥታ ችግር ባሉባቸው አካባቢዎች እንዲጓዙ የሚስገድድ የሥራ ዕድል ሲቀርብላቸው "ምን አለበት ልጆቻችንን ብናሳድግበት…?"የሚል ጥያቄ እስከ ማቅረብ እንዳደረሳቸው ይናገራሉ።

"መኪኖቹ ሒዱና ጫኑ ሲባሉ ሾፌሮቹ ምን አለ ልጆቻችንን ብናሳድግ የሚል ተማጽኖ ሲማጸኑ ይታያል። የማጓጓዣ ኩባንያዎችም በጭራሽ ፈቃደኛ አይሆኑም። ´ንብረታችንን ማጣት አንፈልግም` ይላሉ። ምክንያቱም ከሔዱ መኪኖቹ ላይመለሱ ይችላሉ። ከሰል ድንጋይ የሚወጣው ከመሬት ውስጥ በመሆኑ መቆፈሪያ ማሽኖች ለመከራየት በምንጠይቅበት ጊዜ እንኳን ፈቃደኛ አይሆኑም። ከባድ መኪኖች ምንም ያህል ክፍያ ቢሰጣቸው ገብተው መጫን አይፈልጉም። ምክንያቱም ስጋት አለባቸው። ከአሁን በፊትም ታፍነው የተወሰዱ መኪኖችም ነበሩ" የሚሉት አቶ ረጋሳ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት ይኸ ነው የሚባል መፍትሔ እንዳልተበጀለት ጠቁመዋል።

አንድ ጎማ ስንት ገባ?

ይኸን የደረቅ እና ፈሳሽ ጭነት ማጓጓዣ ዘርፍ የተፈታተነው ግን የጸጥታ መጓደል ብቻ አይደለም። የሥራው  ገቢ እና ወጪ አለመመጣጠን ኹነኛ ፈተና ነው። ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት እና ከጅቡቲ ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ በመጓዝ ላይ የሚገኙት ሾፌር 250 ቶን የመጫን አቅም ያለው ተሽከርካሪ አላቸው። በ1997 በረዳትነት ሥራ ጀምረው ከአራት አመታት በኋላ ሾፌር የሆኑት አሽከርካሪ ሌላ ሰው መቅጠር አዋጪ ሆኖ አልታያቸውም።

አንድ ጊዜ ጅቡቲ ደርሰው ሲመለሱ 58 ሺሕ ብር የሚከፈላቸው አሽከርካሪ "የቻይና ጎማ ከ23 ሺሕ ብር ጀምሮ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሸጠው። በአንጻራዊነት ደህና ነው የሚባለው ጎማ 29 ሺሕ ብር ይሸጣል። ነዳጅ መንግሥት ቢደጉመውም ለእኛ ውድ ነው። ሾፌሩ ደርሶ መልስ 29 ሺሕ ብር ወጪ ይዞ ነው የሚወጣው" ሲሉ ተናግረዋል።

የሰብሪና ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ማጓጓዣ ማሕበር ኃላፊ ወይዘሮ ኑረያ በድሩም ቢሆኑ በዚህ ይስማማሉ። ዘርፉ ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የደም ሥር ሆኖ ቢያገለግልም "የሚረዳውም፣ የሚያግዘውም" አጥቷል የሚል ስሜት የተጫናቸው ወይዘሮ ኑረያ የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ ንረትን ለተጨማሪው ፈተና በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

"አንድ ጎማ 27 ሺሕ ብር ገብቷል። ያንን ወጪ የሚሸፍኑበት ሥራ እየተሰራ አይደለም። በአንድ ወር ውስጥ አንድ የሥራ ጉዞ ነው የሚያደርጉት። በዚያ ላይ ደግሞ ወይ የተሳቢ ኪራይ አለባቸው፤ ወይ የባንክ እዳ አለባቸው። መኪና ከተበላሸ መጠገን አይቻልም። ጎማ ከፈነዳ መግዛት አይቻልም። አንድ ብሎን ከመቶ ምናምን ብር ወደ ሺሕ ሶስት መቶ ብር የገባበት ሰዓት ላይ ነው ያለው። ተሽከርካሪያቸውን ይዘው ጅቡቲ ገብተው አንድን ጭነት ይዘው መምጣት በጣም ከባድ ነው" የሚሉት ወይዘሮ ኑረያ  "የሚያወጡት ወጪ እና የሚያገኙት ገቢ እየተመጣጠነ አይደለም" ሲሉ ምክንያቱን አብራርተዋል።

Dschibuti Tankwagen
በኢትዮጵያ ገበያ የባድ መኪና አንድ ጎማ ከ23 ሺሕ እስከ 29 ሺሕ ብር እንደሚሸጥ በዘርፉ የተሠማሩ ባለሙያዎች ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ምስል Getty Images/S. Gallup

የማጓጓዣው ዘርፍ የተስፋ ጭላንጭል

በኢትዮጵያ ዕቃ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ለማጓጓዝ የሚጠይቀው ወጪም ሆነ የሚፈጀው ጊዜ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ዘርፉ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው። በገቢ እና ወጪ ዕቃዎች ከመነሻ እስከ መድረሻ ባለው ሂደት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ተቆጣጣሪና አገልግሎት ሰጪ አካላት የሚጠየቁ በርካታ የሰነዶች፣ የመረጃና የክፍያ ብዛት፤ የሥራ ሂደቱ የሚወስደው ጊዜ የተንዛዛ መሆን፤ ሥራው በሚጠይቀው ልክ በፋሲሊቲ፣ በመሣሪያና በሰው ኃይል የተሟላ ሆኖ አለመገኘት እና በሎጅስቲክስ ዘርፉ ተዋናዮች መካከል የተቀናጀ አሠራር አለመኖር ማነቆ ሆነው መቆየታቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት የአስር አመት የልማት ዕቅድ ያሳያል። 

ለረዥም አመታት በመዋዕለ-ንዋይ እና የባንክ ዘርፍ የሠሩት አቶ ዮሴፍ ጌታቸው ዘርፉ የተበጣጠሰ መሆኑ ሌላው ፈተና እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ቴክኖሰርቭ በተባለ ተቋም ከፍተኛ ተንታኝ ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙት አቶ ዮሴፍ "በሎጂስቲክስ ዘርፉ በጣም ብዙ ተዋንያን አሉት። ነገር ግን አቅም አላቸው ብለህ የምታነሳቸው ድርጅቶች መቁጠር አትችልም" በማለት በቅጡ አለማደጉን ይናገራሉ። የአገልግሎት አሰጣጡን ቅልጥፍና እንዲጨምር የሚያደርገው የግሉ ዘርፍ ሚና ነው" የሚሉት ባለሙያው የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ፖሊሲ እስኪቀርጽ ድረስ አገሪቱ የምትከተለው ፍኖተ ካርታ "በጣም ውጥንቅጡ የወጣ" ሥርዓት እንደነበር ይተቻሉ። ከዚህ በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ ሚና ውስንነት፣ በመስኩ የተሰማሩ ተቋማት ገንዘብ ባለማግኘታቸው እና ለውጭ መዋዕለ ንዋይ ዝግ ሆኖ መቆየቱ ዕድገቱን የገደቡ ተደራራቢ ምክንያቶች ናቸው።

አቶ ዮሴፍ ዘርፉ በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትም "ብዙ ተስፋ አለው" ባይ ናቸው። ይኸ ተስፋቸው አንድም የሚመነጨው የኢትዮጵያ መንግሥት በሚቀጥሉት አስር አመታት በዘርፉ ተግባራዊ ለማድረግ ከወጠነው ዕቅድ ነው።  "የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀደውን ዕቅድ የሚተገብረው ከሆነ በሚቀጥሉት አስር አመታት ወደ 3 ትሪሊዮን ብር በዚህ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋል። የተለያዩ የፕራይቬት ፐብሊክ ፓርትነርሺፖችን በኢንቨስትመንት መልኩ ኢንቨስት ሊያደርጋቸው ያሰባቸው ብዙ ፕሮጀክቶች አሉ። የዚህን አንድ አስረኛውን እንኳ መተግበር ቢችል ዘርፉን ብዙ ያንቀሳቅሰዋል" ሲሉ ተስፋውን ያስረዳሉ።

አቶ ዮሴፍ የግሉ ክፍለ-ኤኮኖሚ በዘርፉ ያለውን የተገደበ ሚና ለማሻሻል ከኬንያ እና ከናይጄሪያ ልምድ መቅሰም እንደሚገባው ጥቆማ ሰጥተዋል። ሥራውን በቴክኖሎጂ ማዘመን እና የውጭ ወረት ማፈላለግ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች ናቸው። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች፣ የማኅበራት መሪዎች፣ ባለሐብቶች እና በገቢ እና ወጪ ንግድ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚሉት ዘርፉን ላሰጋው የጸጥታ ጉዳይ መፍትሔ ማበጀት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ