1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕአፍሪቃ

መዓከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ታጣቂዎች ግድያ ፈጸሙ

ረቡዕ፣ ሰኔ 26 2016

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በማርቆ ልዩ ወረዳ እና በምሥራቅ መስቃን አዋሳኝ ሥፍራ ላይ ትናንት ታጣቂዎች እናትና ልጅን ጨምሮ ሦስት ሰዎችን ገድለው ሌሎች ሁለት አቆሰሉ ። የአካባቢው ነዋሪዎች ግድያው በታጠቁ ቡድኖች ትናንት ምሽት የተፈጸመው በማረቆ ልዩ ወረዳና በምሥራቅ መስቃን ወረዳ መካከል በምትገኘው ኢንሴኖ ከተማ አቅራቢያ ነው ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4hpdL
ፎቶ፦ ከማረቆ ልዩ ወረዳ መንግሥት ኮሚኒኬሽን የተወሰደ
የማረቆ ከተማ። ፎቶ፦ ከማረቆ ልዩ ወረዳ መንግሥት ኮሚኒኬሽን የተወሰደምስል Mareko district Communication office

ታጣቂዎች እናትና ልጅን ጨምሮ 3 ሰዎችን ገድለዋል

በማዕከላዊ  ኢትዮጵያ  ክልል በማርቆ ልዩ ወረዳ እና በምሥራቅ መስቃን አዋሳኝ ሥፍራ ላይ ትናንት ታጣቂዎች እናትና ልጅን ጨምሮ ሦስት ሰዎችን ገድለው ሌሎች ሁለት አቆሰሉ ። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ግድያው የታጠቁ በተባሉ ቡድኖች ትናንት ምሽት የተፈጸመው በማረቆ ልዩ ወረዳና በምሥራቅ መስቃን ወረዳ መካከል በምትገኘው ኢንሴኖ ከተማ አቅራቢያ ነው ፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ጥቃቱ በሁለት የተለያዩ ሥፍራዎች ግን ደግሞ በተመሳሳይ ሰዓት ላይ ነው የተፈፀመው ፡፡ ግድያው ለወራት ጋብ ብሎ የሰነበተውንአካባቢያዊ ግጭት ሊያባብስ ይችላል  የሚል ሥጋት እንዳደረባቸው ነዋሪዎች እየገለጹ ይገኛሉ ። የሐዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ዝርዝር ዘገባ አለው ።

ዳግም ያገረሸው የማረቆ እና መስቃን አካባቢ ጥቃት

በትናንቱ ጥቃት በታጣቂዎች ከተገደሉት መካከል እናትና ልጅ እንደሚገኙበት ነዋሪዎችና የሟች የቅርብ ዘመዶች ተናግረዋል ፡፡  ምሽት ሁለት ሰዓት አካባቢ ሟቾች በቤታቸው እንደነበሩ የጠቀሱ አንድ የሟች የቅርብ ዘመድ " ሟቾቹ እናት ወይዘሮ አረጉ ቢቂላ እና ልጅ ተማሪ ቅድስት እሸቴ  ይባላሉ ፡፡ ገዳዮቹ በቀጥታ ወደ ቤት ገብተው በመተኮስ ነው እናት እና ልጅን የገደሉት  ፡፡ አገዳደሉም ጭካኔ የተሞላበትና በእያንዳንዳቸው ላይ እስከ አምስት የሚደርስ ጥይት ነው ያርከፈከፉባቸው  ፡፡ በተለይ ተማሪ ቅድስት  የ19 ዓመት ወጣትና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ተፈታኝ ነበረች " ብለዋል ፡፡

ከዚችው የኢንሴኖ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ሌላ መንደር በተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት ደግሞ አንድ መምህር በታጣቂዎቹ በተተኮሰ ጥይት መገደሉን የሟች ወንድም ነኝ ያሉ ነዋሪ ተናግረዋል ፡፡ ወንድሜ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ነበር ከቤት የወጣው ያሉት " ገዳዮቹ መተኩስ ሲጀመሩ ሦስቱም መሸሽ  ጀመሩ ፡፡ ነገር ግን ወንድሜ በጀርባው በገባ ጥይት ተመትቶ ሲሞት ሁለቱ ጓደኞቹ ሮጠው አምልጠዋል " ብለዋል ፡፡

የነዋሪዎች ሥጋት

በማረቆ  ልዩ ወረዳና በምሥራቅ መስቃን ወረዳ  መካከል ባለፉት ዓመታት በዘጠኝ አዋሳኝ ቀበሌያት የይገባኛል ጥያቄ ሲነሳባቸውመቆየቱ ይታወሳል ፡፡ ለበርካታ ሰዎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኖ የቆየው የወሰን መከለል ጥያቄ  ከሁለት ዓመት በፊት በባህላዊ እርቅ ከተቋጨ ወዲህ አካባቢው አንጻራዊ ሰላም ሠፍኖበት ቆይቷል ፡፡ አሁን የተፈጸመው ግድያ በአካባቢው ላይ ዳግም ውጥረት እንዲነግሥ ማድረጉን ነው ነዋሪዎች እየተናገሩ የሚገኙት ፡፡

በመስቃን እና በማረቆ ማህበረሰብ መካከል የተቀሰቀሰ ግጭት
በመስቃን እና በማረቆ ማኅበረሰብ መካከል ከዚህ ቀደም በተቀሰቀሰ ግጭት ላይ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ተቋማት መግለጫ ሰጥተው ያውቃሉ

ዶቼ ቬለ በጥቃቱ ዙሪያ የማረቆም ልዩ ወረዳንም ሆነ የምሥራቅ መስቃን ወረዳ አስተዳዳሪዎችን ለማግኝት ጥረት ቢያደርግም ሃላፊዎቹ የሥልክ ጥሪ ባለመመለሳቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም ።የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል  ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ ግን በአካባቢው በተፈጸመው ጥቃት ላይ የህግ ሥራዎቹን ለመሥራት በሥፍራው ተገኝተው እየገመገሙ መሆኑን በመጥቀስ ዝርዝር ሁኔታን በቀጣይ እንደሚገልጹ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር