1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ዉስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚኖሩ የዉጪ ዜጎች

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 25 2016

አዲስ ፓስፖርት ለማግኘትም ይሁን ነባር ለማደስ ሕዝብን ከከፍተኛ እንግልት እና ምሬት ሊያወጣ እንዳልቻለ በተገልጋዮቹ ክፉኛ የሚነቀፈው የኢምግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ምንም እንኳን በብልሹ አሠራር ተዘፈቁ ያላቸውን ሠራተኞች እና ደላሎችን መያዙን ቢገልጽም ችግሩ አሁንም ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/4arbr
«ኢትዮጵያ ዉስጥ ከ20 ሺሕ የሚበልጡ የዉጪ ዜጎች ያለ ሕጋዊ ሰንድ ይኖራሉ» ሰላማዊት ዳዊት
የኢትዮጵያ የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ ሰላማዊት ዳዊትምስል Solomon Much/DW

ኢትዮጵያ ዉስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚኖሩ የዉጪ ዜጎች

             

ኢትዮጵያ ዉስጥ ሕጋዊ ሠነድ ያልያዙወይም የተጭበረበረ ሰነድ ያላቸዉ  በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የዉጪ ሐገር ዜጎች እንደሚኖሩ የኢትዮጵያ የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት አስታወቀ።የመስሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ ሰላማዊት ዳዊት ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደነገሩት ኢትዮጵያ ዉስጥ ከሚኖሩት የዉጪ ዜጎች መካከል 20 ሺሕ ያሕሉ አንድም ሕጋዊ ሰነድ የላቸዉም፣ አለያም ያላቸዉ ሰነድ የተጭበረበረ ነዉ።በሕገወጥ መረጃና መንገድ ኢትዮጵያ ዉስጥ ይኖራሉ የተባሉትን ሰዎች ሐገር ወይም ዜግነትን ግን አልጠቀሱም።የኢትዮጵያ የኢምግሬሽንና የዜግነት መስሪያ ቤት ለኢትዮጵያዉያንአዳዲስ ፖስፖርትየሚጠይቁ ወይም ለማሳደስ የሚያመለክቱ ኢትዮጵያዉያንን ያንገላታል፣ ሰራተኞቹ ጉቦና ምልጃ ይጠይቃሉ እየተባሉ በተደጋጋሚ ይወቀሳሉ።

በኢትዮጵያ የሕገ ወጥ ሰንዶች መበራከት፣ የውጭ ዜጎች 

አዲስ ፓስፖርት ለማግኘትም ይሁን ነባር ለማደስ ሕዝብን ከከፍተኛ እንግልት እና ምሬት ሊያወጣ እንዳልቻለ በተገልጋዮቹ ክፉኛ የሚነቀፈው የኢምግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ምንም እንኳን በብልሹ አሠራር ተዘፈቁ ያላቸውን ሠራተኞች እና ደላሎችን መያዙን ቢገልጽም ችግሩ አሁንም ቀጥሏል። 

ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ነገር ግን ሕገ ወጥ ሰነድ የያዙ የውጭ ዜጎች ቁጥር አሻቅቧል ሲል አስታውቋል። ሐሠተኛ ቋሚና ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ፣ ሐሰተኛ የፖስፖርት፣ የቪዛ እና የመታወቂያ ሠነዶችን ይዘው የሚኖሩ ሃያ ሺህ የተጠጉ የሌላ ሀገራት ዜጎች መኖራቸው እንደተደረሰበት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ዛሬ አስታውቀዋል። 
"ከ 18 ሺህ በላይ ሐሰተኛ ጊዜያዊ ምኖሪያ ፈቃድ፣ ከ 1500 በላይ ሐሰተኛ ቪዛ ፣ ከ1800 በላይ የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ እንደተገኘ ማየት ችለናል" 

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጉዞ ሰነድ (ፓስፖርት)
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጉዞ ሰነድ (ፓስፖርት)ምስል DW/S. Wegayehu

የአንድ ወር ጊዜ ቀነ ገደብ መሰጠቱ 

እነዚህ ሕጋዊ የመኖሪያ ሠነድ ያልያዙ የውጭ ዜጎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደተቋሙ ቀርበው መስመር እንዲይዙ ያሳሰበው የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ባልተቋቋሙ ድርጅቶች ስም እየገቡ በሕገ ወጥ መንገድ ቪዛ የሚያገኙ የውጭ ዜጎች መበራከታቸውንም አመልክቷል። 
"የካምፓኒ ምዝገባ ሳያከናውኑ ወይም በውሸት የካምፓኒ ስም ተጠቅመው የውጭ ዜጎችን ወደ ሀገር ውስጥ እያስገቡ ባልተፈቀደላቸው የሥራ መስክ ጭምር የሚያሳትፉ እንደሚገኙበት ይዘናል" 

የውጪ ሀገራት ዜጎችን ሕጋዊነት የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት ይሄው ተቋም እንዴት እንደገቡ አገባባቸው የማይታወቅ የውጭ ዜጎች መኖራቸውንም ደርሼበታለሁ ብሏል። 

የፓስፖርት አገልግሎት እና ሊቀረፍ ያልቻለው እንግልት 

ከፓስፓርትእድሳትም ይሁን አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በሌብነትና ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ ሕዝብን ያማረሩ ያላቸውን 38 የተቋሙን ሰራተኞችን እና 15 ደላሎችን ከዚህ በፊት መያዙን የገለፀው ተቋሙ ሕገ ወጥ መታወቂያ ይዘው የሚገኙ የውጭ ዜጎች ቁጥርም በአሳሳቢ ሆኔታ እየጨመረ መሆኑን አስታውቆ ነበር። ዘላቂ መፍትሔውንም ዋና ዳይሬክተሯ አመልክተዋል። 
"በአጭር ጊዜ ውስጥ ምናልባት የኢትዮጵያፓስፖርት የሚቀየርበት እና ወደ ኤሌክትሮኒክስ ፓስፖርት የሚገባበትን እየሠራን ነው" 
ኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ በስደተኝነት የሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎችን የማይመለከት መሆኑን ገልጿል።

 

ሰለሞን ሙጬ 

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር