ሔልሙት ኮል፤ የስልጣን ታሪክ
በጎርጎረሳዊዉ 1989 ዓ.ም የኮል የፖለቲካ ሕይወት ወደ ማብቅያዉ እያዘነበለ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሌላ አቅጣጫ ታሪካዊ ንፋስ ነፈሰ። ሔልሙት ኮልም ይህን ታሪካዊ ክስተት ተቆናጠዉ ያዙ። ከዝያም ለ 6ኛዉ የጀርመን መራሄ መንግሥት ሔልሙት ኮል የጀርመንና የአዉሮጳ ፖለቲካ ቅርስ ሆኖ ቆመ።
ሰፊ የሕይወት እቅድ
ኮል ገና ከመጀመርያዉ ምን እንደሚፈልጉ ያዉቁ ነበር። የጀርመን የመጀመርያዉ መራሔ መንግሥት የኮነራድ አደናወር ፍልስፍና ተከታይ ቢሆኑም ራሳቸዉን የመጀመርያዉ መራሄ መንግሥት ወራሽ አድርገዉ ቆጥረዉ አያዉቁም። ይሁንና የአደናወርን ተፅእኖ ከመጀመርያዉ ጀምሮ ያዉቁት ነበር። በራይን ላንድፋልስ ግዛት ዓመታዊዉ የሶሻልዴሞክራቶች ኅብረት ፓርቲ የ«CDU» ስብሰባ ሲካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔተርአልት ማየርን ድጋፍ አድርገዉ፤መራሔ መንግሥት አደናወርን ጋብዘዋቸዉ ነበር። አደናወር ግብዣዉን ተቀብለዉ ተገኝተዋል። ይህ ክስተት የፖለቲካ ጉዞአቸዉን አንድ ደረጃን ከፍ ያደረገ ነበር።
የቤተሰብ ታሪክ ? ጥሩ ሆኖ አግንቸዋለሁ!
ሔልሙት ኮል ከጊዜዉ ጋር የሚሄዱ አዲስ ነገር ፈጣሪ ናቸዉ። ዋንኛ የተባሉ የመገናኛ ብዙኃኖች ኮልን በራይንላንድ ፋልስ ግዛት ፖለቲከኛ ሆነዉ ያገኝዋቸዉ በ 1970ዎቹ መጀመርያ ላይ ነበር። ለጋዜጠኞች ኦገርስሃይም የሚገኘዉን ቤታቸዉን በር ለተደጋጋሚ ጊዜ ይከፍቱም ነበር። በዝያን ጊዜ ስለ ቤተሰብ አባቱ ስለ ፖለቲከኛዉ ይወጣ የነበረዉ ዘገባ ሁሉ የኮልን ስብዕና በጥሩ የሚያሳይ ነበር። ኮል ታታሪ ሰራተኛ ፤ ፈጣን እና በጊዜያቸዉ አርቆ አሳቢ ስብዕናን የተላበሱ ነበሩ።
መራሔ መንግሥት ለመሆን በቁ!
በጎርጎረሳዊዉ ጥቅምት 1, 1982 ዓ.ም ሔልሙት ኮል በፖለቲካ ጉዞአቸዉ ሲያልሙት እነበረዉ ዓላማ ላይ ደረሱ። ከአንዲት ትንሽ ገጠር ከተማ የመጣዉ የዝያን ጊዜዉ ወጣት ፖለቲከኛ ኮል፤ የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ አባል «SPD» ፤ የዓለም ፖለቲከኛዉንና የዝያን ጊዜዉን የጀርመን መራሔ መንግሥት ሄልሙት ሽሚትድን ተኩ። በዚህ ሰዓት ኮል የግራ ክንፎች ይሳለቁባቸዉና ይቀልዱባቸዉ ነበር። ብዙዎች ኮል የተላበሱትን ከፍተኛ የፖለቲካ እዉቀትና ሚዛን ላይ አላስቀመጡም ነበር። ዉሳኔያቸዉን የማያጥፉ መሆናቸዉንም ጠንቅቀዉ አላወቁም ነበር።
የወቅቱ ስሜታዊዉ ነጸብራቅ
በጎርጎረሳዊ መስከረም 22፤ 1984 ዓ.ም ፈረንሳይና ጀርመን በ 2ኛዉ ዓለም ጦርነት ከፍተኛ ዉግያ ባካሄዱበት በሰሜን ምዕራብ ፈረንሳይ ፈርዱን በተባለ ቦታ ነበር። ማን ለማን እጁን ለሰላም ዘረጋ? የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ሚትሯዋ እና ሄልሙት ኮል የጀርመንና የፈረንሳይ ወታደሮች በወደቁበት ቦታ የማይረሳ ታሪክ ሰሩ። ይህ ታሪክ መራሔ መንግሥት ቪሊ ብራንት ዋርሶ ፖላንድ ላይ ተንበርክከዉ ይቅርታ ከጠየቁበት ታሪክ ጋር ይመሳሰላል።
በ1989 ዓ.ም አብቅቶላቸዉ ነበር
በጎርጎረሳዊዉ መስከረም 1989 ዓ.ም በብሪመን በተካሄደዉ የክርስትያን ዴሞክራቶች ኅብረት ፓርቲ «CDU» ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የሔልሙት ኮል የፖለቲካ ጉዞ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። የጤና እክል አጋጥሞአቸዉ የነበሩት ኮልን፤ ታዋቂ የፖለቲካ ፓርቲ አጋሮቻቸዉ ከፓርቲ መሪነት ሊያነሱዋቸዉ ቢሞክሩም ተቋቁመዉ ችግሩን ማለፍ ችለዋል። ከዚህ ቀደም ሲል ሃንጋሪ በሽዎች ለሚቆጠሩ የምስራቅ ጀርመን ስደተኞች ድንበርዋን እንደከፈተች መረጃዉ ደርስዋቸዉ ነበር። የከሸፈዉ ኮልን ከፓርቲያቸዉ መሪነት የማንሳት ሙከራ ለኮል አዲስ የፖለቲካ እድል ይዞላቸዉ መጣ።
"ይህ ታሪካዊ ሰዓት ሲመጣ ..."
ይህ ታሪካዊ ሰዓት ሲመጣ ... በጎርጎረሳዊዉ ታሕሳስ 1989 ዓ.ም የጀርመናዉያን የዉሕደት ጥያቄ ገና መልስ አላገኘም። ሔልሙት ኮል የሚገኙት በድሬስደን ከተማ ነበር። የዉሕደቱ ወሪም ይናፈሳል።በድሪስደን አደባባይ የነበረዉ ሕዝብ ኮል የጥያቄዉን መልስ ይሰጡ ይሆን የሚል ጥያቄ ነበረዉ። ኮል ትንሽ ጠበቁ፤ በኋላም ዓላማዉን ተናገሩ ፤ እንዲህ ሲሉ «ዓላማችን የጀርመኖች አንድነት ነዉ»። በደስታ የሚቦርቁ በ 10 ሽዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦች መሃልም ተገኙ።
ለጀርመን ዉሕደት በሹራብ ጃኬት
በጎርጎረሳዊዉ 1990 ዓ.ም ከሐምሌ 14 እስከ 16 በተደረገዉ ድርድር ሁለቱ ጀርመኞች ተዋሃዱ። ኮልና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሃንስ ዲትሪሽ ጌንሸር በሞስኮ እና በጎርቫቾቭ የትዉልድ ቦታ ካቭካዝ ዉስጥ ነበሩ። ሁለቱ ፖለቲከኞች ወድዝያ ያቀኑት ኔቶ የተዋሐደችዉን ጀርመን ይቀበላል አይቀበልም የሚለዉን ጥያቄ ይዘዉ ነበር። ጎርባቾቭ ዉሕደቱን በአዎንታ ተቀበሉት። ይህ ጥያቄ በጀርመን የዉሕደት ጉዞ የመጨረሻዉ የፖለቲካ መሰናክል ነበር።
ጠንካራዉ ሰዉ
ሔልሙት ኮል ያሰቡትን ለማሳካት ጉልበት አንሶአቸዉ አያዉቅም። በቁመናቸዉ ርዝመትና በፖለቲካ አቋማቸዉ «ጥቁሩ ግዙፍ» ሲሉም ይጠሩዋቸዉ ነበር። ኮል ራሳቸዉን በሚገባ ሁኔታ መከላከል የሚችሉም ነበሩ። ግንቦት 10 ሐለ በሚባል የጀርመን ከተማ ዉስጥ የተቃዉሞ ሰልፈኞች ሔልሙት ኮል ላይ እንቁላል ወርዉረዉ ጥቃት ሲፈፅሙባቸዉ ኮል ከሰልፈኞቹ ጋር ትግል ሊገጥሙ ወደ ሰልፈኞቹ በኃይል ሲጠጉ፤ የግል ጠባቅያቸዉ ከኋላ ጎትተዉ መልሰዋቸዋል። ኮል ወደ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ በመቅረብ ችግሩን በጉልበትለመፍታት ፈልገዉ ነበር።
ጀርመንን አዉሮጳ ማድረግ
ሔልሙት ኮል ከልብ የሚወዱት አዉሮጳ ለርሳቸዉ የፖለቲካ ሜዳ አልነበረም። ለጉብኝት ያኔ የምዕራብ ጀርመኑ ዋና ከተማ ቦን የመጡት የአዉሮጳ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ያኩስ ዴሎርስ ኮል አዲሱን የአዉሮጳ ካርታ ለኮል ሲሰጥዋቸዉ የጀርመን ዉሕደት ገና ተወሰነ እንጂ በይፋ ድግስ አልተከበረም ነበር። ካርታዉ የተዋሃደችዉ ጀርመን የአዉሮጳ ሕብረት አባል መሆንዋን የሚያሳይ ነበር።
የቤተሰብ ጉዳይ
በጎርጎረሳዉያኑ 2001 ዓ.ም የኮል ባለቤት ሃነሎረ ኮል ከብዙ ጊዜ ሕመም በኋላ ሕይወታቸዉን በገዛ እጃቸዉ አጠፉ። ከሃነሎረ ሞት በኋላ የኮል የፖለቲካና የቤተሰብ ሕይወት አደባባይ ወጣ። ከዛም ቤተሰቡ በጸብ ተበተነ። «የአባቴ ሥራ ፀባይ በቤተሰቡ ሕይወት ላይ ተፅኖ አሳድሮ ነበር ብዬ ብናገር አላጋነንኩም» ሲሉ ልጃቸዉ ቫልተር ኮል «መኖር ወይስ መወደድ» ሲሉ ባሳተሙት መጽሐፍ የቤተሰባቸዉን ታሪክ አስቀምጠዋል።
የኮል የቅርብ ወዳጆች
ኮል በጥሩ ሁኔታ የቀረባቸዉን ሁሉ ያስታዉሳሉ።ኮል ገና ከመጀመርያዉ በወጣትዋ ፖለቲከኛ አንጌላ ሜርክል ላይ ዓይናቸዉን አሳርፈዉ ነበር። ሜርክልም ቢሆኑ ለረጅም ጊዜ በኮል ከለላ ስር ነበሩ። ኮል ለፓርቲያዉ «CDU» በሚስጥር ከነማን በሚሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ስጦታ እደተቀበሉ በግልጽ መናገር አልፈለጉም። በዚህ የተነሳም ሜርክልና ኮል ወዳጅነታቸዉ አበቃ። ኮልም በመጨረሻ ብሔራዊ ሽልማት ሲበረከትላቸዉ ሜርክል ንግግር እዲያደርጉ ፈቃዳቸዉ ሳይሆን ቀረ።
ማይከ ሪሽተር-ኮል
ከጎርጎረሳዉያኑ 2005 ጀምሮ በይፋ ፍቅረኛቸዉ መሆናቸዉ ከተነገረዉ ከማይከ ሪሽተር ጋር ኮል ከሦስት ዓመት በኋላ ትዳር መሰረቱ። የኮል አዲስዋ የትዳር አጋር ግን በፊትም አሁንም አወዛጋቢ ናቸዉ። የ 53 ዓመትዋ የምጣኔ ሐብት ምሁር ማይከ ሪሽተር-ኮል የባለቤታቸዉ የኮል ዋና ተቆጣጣሪና በሁሉ ነገር ወሳኝዋ ሆኑ ተብለዉ ተወቅሰዋል። ሔልሙት ኮል ከሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸዉ ሊለያዩ የበቁትም በሳቸዉ ምክንያት ነዉ ተብለዉም ይታማሉ። ዙድ ዶይቼ ሳይቱንግ የተሰኘዉ ጋዜጣ «የኮል የጤና ረዳት፤ ከለላና ተቆጣጣሪ » ሲል በ 2012 ዓ.ም አስነብቦአል።