ሐረር ሰላማዊዋ ከተማ
ጥንታዊ ታሪክን የያዘችዉ ሐረር ከተማ የተለያዩ ሃይማኖቶችን አቅፋ በመያዝዋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ 2006 ዓ.ም ጀምሮ በጥበቃ ሰንጠረዥ ዉስጥ አካቷታል። የዶቼ ቬለዋ «DW» ባልደረባ ማሪያ ጌርት ኒኩሌሱኩ ሃረር ከተማ ተዘዋዉራ የተመለካከትችዉን በፎቶ አስደግፋ ዘገባ ሰርታለች።
ሐረር ጀጎል፤ ምስራቃዊትዋ ጥንታዊት ከተማ
ታሪካዊትዋ ሐረር ከተማ በ 10ኛዉ እና በ 13ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ወደ አካባቢዉ በፈለሱ አረቦች እንደ ተቆረቆረች ይነገራል። ወደ ከተማዋ ጥንታዊ ክፍል ጀጎል ዘልቆ ለመግባት ከአምስቱ በሮች አንዱን በር መጠቀም የግድ ይላል። የኢትዮጵያ አነስተኛ ግዛት የሆነዉ የሐገርጌ መዲና ሐረር በአብዛኛዉ የኦሮሞኛ ተናጋሪዎች መኖርያም ነች። የኢትዮጵያ ምስራቃዊ ከተማ ሐረር ከጎርጎረሳዉያኑ 2006 ዓ.ም ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት የትምሕርት፥ የሳይንስና የባሕል ድርጅት «UNESCO» ጥበቃ ስር ትገኛለች።
ሙስሊሞች በሐረር
እነደ መንግሥታቱ የቅርስ ጥበቃ ድርጅት ሐረር የሙስሊሞች አራተኛዋ ቅዱስ ከተማ ናት። ከተማዋ 82 መስጂድ እንዲሁም ከ 100 በላይ አዛንን ይዛለች። «ጃሚዕ» በሐረር ትልቁ መስጂድ ነዉ። በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከተሞች በተለይ ሐረር ከተማ አብዛኛዉ ነዋሪ ሙስሊም እንደሆን ነዉ የሚነገረዉ።
የሴቶች መስጂድ
«ጃሚዕ መስጂድ» ሴቶችም ወንዶችም በአንድ ላይ ፀሎት ማድረስ የሚችሉበት ብቸኛዉ መስጂድ ነዉ። በጃሚዕ መስጂድ የሴቶች ፀሎት ክፍል በቀኝ በኩል ባለ አነስተኛ በር በኩል በማለፍ ይገኛል። በከተማዋ የሚገኙ ሌሎቹ መስጂዶች በጣም አነስተኛ በመሆናቸዉ በአብዛኛዉ ወንዶች ብቻ ነዉ የሚገኙበት። ጃሚዕ መስጂድ በምዕመናን ከሞላና ቦታ ከጠፋ ወንዶችም ሴቶችም ምዕመናን ግቢ ዉስጥ ፀሎት ሲያደርሱ ይታያል።
ሰላማዊዋ ከተማ ሐረር
በሐረር ከሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያኖች መካከል ቅዱስ መድሐንያለም ቤተ-ክርስያን አንዱ ነዉ። ሐረር በማኅበረሰብ አብሮነት ገፅታዋ ምክንያት ዩኔስኮ በጎርጎረሳዉያኑ 2003 ዓ.ም ሰላማዊ ከተማ ሲል እዉቅና ሰጥቷታል። ሐረር ከተማ የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮችን እጅዋን ከፍታ በመቀበልዋ ምክንያት ነዋሪዎችዋም ይኮራሉ። የሐረር ከተማ የፖለቲካ ተወካይና የመሪት ይዞታን በተመለከተ ባለፉት ዓመታት ዉጥረት ተስተዉሎባታል።
የሐረር ታሪካዊ እዉነቶች
120 ሕዝብ በሚኖርባት ሐረር የተለያዩ ታሪካዊ እዉነቶች የሚተረኩባት ከተማ ናት። ለዚህ እንደምክንያት የሚጠቀሰዉ የሱፊ እስልምና ያሳደረዉ ተፅኖ እንደሆነ ይታመናል። በከተማይቱ እጅግ ከሚከበሩ አካባቢዎች አንዱ የሼህ አባድር የቀብር ስፍራ ይገኛል። ሼህ አባድር የከተማይቱ አንዱ መስራች ናቸዉ ተብሎም ይታመናል። በሼህ አባድር በመካነ መቃብር አካባቢ ሰዎች ተሰብስበዉ ጫት ሲቅሙ ማየት የተለመደ ነዉ።
ታዋቂዉ ቅጠል
በቀደሙት ዓመታት ጫት ለመንፈሳዊ ጥቅም ይዉል እንደነበር ይነገራል። ጫት በመላ ኢትዮጵያ ይታወቃል በብዙ አካባቢዎችም ይቃማል። ከፍተኛዉ የጫት ንግድና ጫት ጥቅም ላይ ሲዉል የሚታየዉ ግን በሐረር ከተማ ዉስጥ እንደሆነ ነዉ የሚነገረዉ። የሐረር ከተማ ከፍተኛ የንግድ ገቢ የሚገኘዉም ከጫት ነዉ። የከተማዋ ነዋሪዎችም በአብዛኛዉ በየቀኑ ጫትን ይቅማሉ።
የጨርቃ ጨርቅ ንግድ
የሐረር ምጣኔ ኃብት ልዩ በሆነ ገበያ የሚደገፍ ነዉ። የጨርቃ ጨርቅ ገበያ እና የልብስ ሰፊዎች በሚገኙበት መንገድ ላይ ከልብስ ስፊዎች መኪና የሚወጣዉን ድምፅ ተከትሎ መንገዱ «መኪና ግርግር» የሚል መጠርያ ተሰቶታል። በአብዛኛዉ ከሐረር ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች ወደ «መኪና ግርግር» ከመጡ ለቀሚስ የሚሆን ጨርቅን ገዝተዉ እና አሰፍተዉ ነዉ የሚመለሱት።
የሐረር ገበያ
ከሐረር ከተማ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ለገበያ የሚያቀርቡትን ሸቀጦች በአህያ ጭነዉ ሰዓታትን ተጉዘዉ ወደ ጀጎል ይመጣሉ። በገበያዉ ቦታ የቤት እቃዊዎች፤ አልባሳት፤ ሥጋን እና ቅመማ ቅመን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ አይነቶች እና ጥራጥሪዎችን ማግኘትና መሸመት ይቻላል።
የግመል ንግድ
ከሐረር ከተማ 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝዉ ቦታ ላይ የግመል ንግድ ይካሄዳል። በሳምንት ሁለት ጊዜ በሚቆመዉና ታዋቂ በሆነዉ በዚህ የግመል ገበያ ማለዳ ላይ ብቻ እስከ 200 ግመሎች ይሸጣሉ። በግመል ገበያዉ ላይ ትንሹ የግመል ዋጋ 20 ሺህ ብር እንደሚወጣ ይነገራል። ለሽያጭ የሚቀርቡትና ለምግብነት አልያም ለማመላለሻ አገልግሎት የሚዉሉት ግመሎችን ለንግድ የሚያቀርቡት ሶማሌ አርብቶ አደሮች ናቸዉ።