1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 ልጆችና ሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ሰኔ 3 2012

ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ ኮሮና ተሐዋሲ ካስከተለው እንቅስቃሴ ላይ የተጣለ ገደብ ጋር በተያያዘ 101 ልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ለእነሱ የቅርብ በሆኑ ወገኖች መፈጸሙ በይፋ ከተሰማ ወዲህ ጉዳዩ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ከዚህ ቀደምም ጥቂት የማይባሉ በርካታ መሰል ድርጊቶች በሕግ ባለሙያዎችና የመብት ተሟጋቾች ዘንድ ተመዝግበዋል።

https://p.dw.com/p/3dacb
Symbolbild Protest gegen Vergewaltigung
ምስል picture-alliance/Pacific Press/E. McGregor

«ዝም አንልም የሚል ዘመቻ ተጀምሯል»

የወትሮን እንቅስቃሴና ተግባራት ያሰነካከለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በየቤቱ ፆታዊም ሆነ ወሲባዊ ጥቃቶች እንዲበራከቱ ማድረጉ እየተነገረ ነው። አዲስ አበባ ላይ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ልጆች የዚህ ጥቃት ሰለባ የመሆናቸው ዜና እንዲህ ያለው ወንጀል የሚዳኝበት ሂደትም ሆነ የሚሰጠው ትኩረት እንዲጤን የሚያሳስብ መሆኑን የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪዎችና የሕግ ባለሙያዎች ለዶቼ ቬለ አመልክተዋል። ይፋ የሆነው አሃዝ በአዲስ አበባ የተፈጸመው ብቻ ነው መባሉ ደግሞ ችግሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምን ሊመልስል እንደሚችል አሳሳቢ መሆኑንም ጠቁመዋል። ሸዋዬ ለገሠ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች።
ከሰሞኑ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ኮሮና ተሐዋሲ ካስከተለው እንቅስቃሴ ላይ የተጣለ ገደብ ጋር በተያያዘ 101 ልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ለእነሱ የቅርብ በሆኑ ወገኖች መፈጸሙ በይፋ ከተሰማ ወዲህ ጉዳዩ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ከዚህ ቀደምም ጥቂት የማይባሉ በርካታ መሰል ድርጊቶች በሕግ ባለሙያዎችና የመብት ተሟጋቾች ዘንድ ተመዝግበዋል። የሰሞኑ መረጃ ግን በማኅበራዊ መገናኛዎች ሳይቀር ዝም አልልም የሚል ዘመቻን አንቀሳቅሷል። የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሕብረት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መስዑድ ገበየሁ የሕግ ባለሙያና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ናቸው። ከዚህ ቀደም ጥቃቶቹ ይፈጸሙበት የነበረበት ስፍራና ሁኔታ ከአሁኑ የተለየ በመሆኑ ትኩረት እንዲያገኝ እንዳደረገው ነው የገለፁልን።
የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ይህን ጉዳይ ይፋ ካደረገ በኋላ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት መዓዛ አሸናፊ በትዊተር ያሰራጩት መረጃ እንደሚያመለክተው ጉዳዩ ወደ ፍትህ አካላት አለመድረሱን ነው። ፕሬዝደንቷ እንደሚሉትም ምንም እንኳን በፌደራል ፍርድ ቤቶች የሴቶችና ሕጻናትን ጉዳዮች የሚያዩት ችሎቶች በኮቪድ 19 ምክንያት ባይዘጉም ክስ መከፈቱን የሚያመላክቱ መዛግብት አልተገኙም። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በፌስቡክ ገጹ ያወጣው መረጃ ደግሞ 94 መዝገቦች በፖሊስ ምርመራ ላይ መሆናቸውና 23 ክሶች መመሥረታቸውን እንዲሁም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 4 መዝገቦች ላይ የፍርድ ውሳኔ መሰጠቱን ያመለክታል። ፆታዊ ጥቃቶችን መከላከል ላይ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ሴታዊት የተሰኘው ድርጅት መሥራች እና አስተባባሪ ዶክተር ስሒን ተፈራ እንዲህ ያሉ ጥቃቶች ተድበስበው የሚቀሩበት ስፍራ አለ ባይ ናቸው። 
ከሰሞኑ ይፋ የሆነው ለወሲባዊ ጥቃት የተጋለጡ ልጆች ቁጥር የኅብረተሰቡን ቀልብ በመሳቡና ይህ ችግር ጠበቅ ያለ ሕግዊ  መፍትሄ እንዲኖረው ብዙዎች በዘመቻና ቅስቀሳ መልክ ሳይቀር ለመጠየቅ መሞከራቸው አበረታች ነው ያሉት ዶክተር ስሒን፤ እሳቸው የሚመሩት ድርጅት ከሕግ ባለሙያ ሴቶች ጋር በመሆን ጉዳዩ በጥንቃቄ እንዲታይ እየሠሩ መሆኑንም ገልጸዋል። እንዲህ ያሉ ወሲባዊ ጥቃቶችም ሆኑ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ተባብሰው ለመቀጠላቸው የሚወሰደው የቅጣት ርምጃ የላላ ስለሆነው የሚሉ ወገኖች ጥቂት አይደሉም። የሕግ ባለሙያና የሰብያዊ መብት ተሟጋች የሆኑት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሕብረት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መስዑድ ገበየሁም ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያላቸው። 
የሕግ ባለሙያዎቹ እንደገለፁልን እነሱ በየዕለት ሥራቸው ከተጎጂዎች የሚደርሷቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀሙ ወሲባዊም ሆነ ፆታዊ ጥቃቶች ጥቂት አይደሉም። ከሰሞኑም በአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ በኩል ይፋ የተደረገው ቁጥር የሚያመለክተው የተሻለ መረጃና ግንዛቤ ያለው ኅብረተሰብ ይኖርባታል ተብሎ በምትገመተው በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ብቻ መሆኑን ልብ ይሏል። ጉዳዩን አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ጥቃት የተፈጸመባቸው ወገኖች ከሕግም ሆነ ከደረሰባቸው አካላዊና ስነልቡናዊ ጉዳት ለማገገም እንዲረዳቸው ሊያገኙት የሚገባውን አገልግሎት ማመቻቸት ላይ አተኩሮ እየተሠራ ነው። 

Symbolbild Frankreich Justiz
ምስል Getty Images/AFP/L. Venace
Äthiopien Addis Abeba
ምስል DW/S. Muchie

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ