1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወጣቶች ዓለም

ዓርብ፣ መስከረም 14 2014

ለአካል ጉዳታቸው የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ቢሟሉላቸው የሚፈልጉትን ነገር በሙሉ ከሌሎች እኩል ሆነው መሥራት እንደሚችሉ ዛሬ እንግዳ ያደረግናቸው ሦስት ዐይነ-ስውራን ወጣቶች ይናገራሉ። ወጣቶቹ በምን አይነት ሁኔታ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ እና ምን አይነት ድጋፍ እንደሚሹም ገልፀውልናል።

https://p.dw.com/p/40nfW
Afrika Kinder in Burundi
ምስል Jesko Johannsen

የወጣቶች ዓለም

እንደ  የዓለም የጤና ድርጅት ከሆነ በዓለም ላይ 43 ሚሊዮን የሚሆኑ ዐይነ-ስውራን ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል 17 ሚሊዮን የሚሆኑት ለዐይነ ስውርነት የተዳረጉት ሊስተካከል ወይም ሊገፈፍ በሚችል የዐይን ሞራ አማካኝነት እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሌላው ችግር ደግሞ አብዛኞቹ ማለትም 90 በመቶ ያህሉ የሚኖሩት ባላደጉ ወይም በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት ነው።  ዘካሪያስ መንግስቱ ደሴ ከተማ ውስጥ የሚኖር የ12 ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ዐይነ  ስውር የሆነው ገና በህፃንነቱ እንደሆነ ነው የሚያውቀው« እናት እና አባቴ የሚሉት ከአራት አመቴ ጀምሮ እንደዚህ እንደሆንኩ ነው»  ያደኩትም ገጠር ስለነበር  ምክንያቱ አልታወቀልኝም ነበር ይላል ዘካሪያስ።
የ8ኛ ክፍል ተማሪዋ አባይነሽ ጌትነት ስትወለድ አንስቶ ዐይነ ስውር ናት። 17 ዓመቷ ነው።  « ህክምናም ፀበልም ሞክሬያለሁ እስካሁን ግን አልተፈወስኩም» የምትለው አባይነሽ እሷም ገጠር አካባቢ በመኖሯ እና ወላጆቿ ደሀ ስለነበሩ በጊዜ ወደ ትምህርት ቤት አልገባችም። ትምህርት ቤትም የገባችም ለህክምና ደሴ ከተማ በሄደችበት ወቅት ነው። 
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት በድህነት እና በገጠማቸው የአካል ጉዳት አማካኝነት ተምረው ራሳቸውን የሚችሉ አካል ጉዳተኞች ውስን ናቸው። ዘካሪያስ የትምህርት እድል እንኳን እስኪያገኝ ብዙ ጊዜ ፈጅቶበታል።  « ከገጠር ወደ ከተማ የሄድኩት የቤተ ክህነት ትምህርቴን ለማጠንከር ነበር። ከዛ ዘመናዊ ትምህርት እንዳለ ነገሩኝ። እኔም ሁለቱን ጎን ለጎን መከታተል ጀመርኩኝ። በዚህም የተነሳ እድሜዬ  ወደ 30ዎቹ ይደርሷል» ይላል። ወጣቱ ወደፊት የህግ ባለሙያ መሆን ይፈልጋል።
ዘካሪያስ፣  አባይነሽ እና ይባቤ ይሄይስ ይተዋወቃሉ። ከሌሎች ዐይነ ስውራን ጋር በመሆን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዐይነ ስውራን ማኅበር የደሴ ቅርንጫፍን መስርተዋል። ማኅበሩ የተመሠረተው ከሁለት ዓመት በፊት በ2012 ዓ.ም ሲሆን፤ ከዚያ በፊት «መብታችን ይከበር ለማለት እንኳን ለማን አቤት ማለት እንደነበረብን ዐናውቅም ነበር » ይላል ይባቤ። የዚህ ማህበርም አላማ« ደሴ ከተማ የሚኖሩ አይነ ስውራንን መብት፣ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ነው። » ከዚህም ሌላ የአይነ ስውራንን ንቃተ ህሊና ከፍ ለማድረግ ነው።» ይላል ይባቤ። በ40 አባላት የተመሠረተው ማህበር በአሁኑ ወቅት 122 አባላት አሉት። እነሱም በተለያየ እድሜ እና የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ አይነ ስውራን ናቸው።

Äthiopien | Sebat bet Agew Festival in Injibara
አይነ ስውሩ ፈረስ ጋላቢ ምስል Alemnew Mekonnen/DW

አባይነሽ መንገድ ዳር ሶፍት እና የጥፍር መቁረጫ  እየሸጠች ነው የራሷን እና የ5 ዓመት ልጅዋን ሕይወት የምታስተዳድረው። ይሁንና ኮሮና ከገባ በኋላ ገበያው ተቀዛቅዟል ትላለች። አሁን ደግሞ በሀገሪቱ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ነገሮችን አባብሶባቸዋል። « በጣም ችግር ላይ ነኝ። በዚህ የተነሳ ልጄን በዚህ አመት ትምህርት ቤት እንኳን አላስገባኋትም። » አባይነሽ በዚህ አስቸጋሪ ሕይወቷ በልጅነቷ ልጅ ለመውለድ የወሰነችው በመሪ ችግር ነው ትላለች። « እኔን እየመራችንኝ የተለያየ ቦታ ልታደርሰኝ ትችላለች።  ተምራ ስትለወጥ ለእኔም አንባቢ ትሆናለች፤ እገዛ ታደርግልኛለች። እና እኔ ብወልድ የራሴ ያልኩት ይኖርኛል ብዬ ነው  ለመውለድ በራሴ እሳቤ የወሰንኩት። 
አባይነሽ ወደፊት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አልያም የስነ ልቦና የምክር አገልግሎት ለጋሽ ሆና ራሷን እና ወገኗን መጥቀም ትፈልጋለች።  ዐይነ ስውራኑ ወጣቶች ኑሮን ለማሸነፍ ከሚያደርጉት ትግል ባሻገር ስለሚገጥማቸው ፈተና እና ዓይናማ ሰዎች ማድረግ ይገባቸዋል ስለሚሉትም ገልፀውልናል። ዘካሪያስ 12ኛ ክፍል እስኪደርስ ማስቲካ እና የስልክ ካርድ እያዞረ በመሸጥ ነው ራሱን እያስተዳደረ ያለው። የሚያስቸግረው ነገር ትምህርት ቤት ውስጥ ለአይነ ስውራን የሚሆኑ መገልገያዎች አለመሟላታቸው ነው። « ሌሎች አይናማ ተማሪዎች በስክሪብቶ ፅፈው ደብተር አንብበው ፈተና ሲፅፉ እና እኛ አይነ ስውራን ግን መምህሩ ሲያስተምር በቃል ብቻ አዳምጠን  ነው ፈተና የምንፈተነው። በዛ ላይ ሌሎቹ  ሶስት አራት ጊዜ ፈተና ሲፈተኑ እኛ በቃል አንድ ጊዜ ብቻ የምንፈተንበት ሁኔታ አለ» ቢሆንም ግን አይነ ስውራኑ መፍትሄ አላጡም። አይናማ ልጆችን አንብቡልን እያሉ እና መምህሩ የሚያስተምሩትን በድምፅ እየቀረፁ እንደሚያጠኑ ዘካሪያስ ይናገራል። አባይነሽ ደግሞ« ከኛ ራቅ ብለው ከመፈረጅ ይልቅ ቀርበው ቢያናግሩን ችግራችንን ይረዳሉ። ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ ምንድን ነው ብለው ቢረዱን ጥሩ ነው» ትላለች።


ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ