1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

«እየተተኮሰብን ነው አምልጠን የወጣነው » ሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን

ልደት አበበ
ዓርብ፣ መስከረም 24 2017

የእሥራኤል ጦር ሰሞኑን ሊባኖስ ውስጥ የሚገኘውን የሂዝቦላህ ቡድን ለማጥቃት የከፈተውን መጠነ ሰፊ ውጊያ ሸሽተው ከ1 ,2 ሚሊዮን በላይ ሊባኖሳውያን መፈናቀላቸው ተሰምቷል። በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው ለመስራት ወደ ሊባኖስ የሄዱ እንደ የኢትዮጵያ፣ ፊሊፒንስ፣ ሲሪላንካ እና የሱዳን ሀገር ዜጎችም ከመፈናቀል እና መሰደድ አልዳኑም።

https://p.dw.com/p/4lNYV
ከእስራኤል ጥቃት በኋላ ሊባኖስ ውስጥ ጎዳና ላይ የተፈናቀሉ
ከእስራኤል ጥቃት በኋላ ሊባኖስ ውስጥ ጎዳና ላይ የተፈናቀሉምስል JOSEPH EID/AFP

«እየተተኮሰብን ነው አምልጠን የወጣነው » ሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን

የመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት በአሳሳቢ ደረጃ ተባብሶ ቀጥሏል። እስራኤል የሂዝቦላህ ቡድንን ለማጥቃት በምድር ጭምር ካለፈው ማክሰኞ አንስቶ ወደ ሊባኖስ ስትዘምት፤ የሂዝቦላህ ቡድንን የምትደግፈው ኢራን ሚሳኤሎቿን ወደ እስራኤል  አስወንጭፋለች። 
የእሥራኤል ጦር ኢላማዎቹን ማጥቃት ቀጥሏል። ለደህንነታቸው ሲሉ የደቡባዊ ሊባኖስ ነዋሪዎች  20 ከተሞችን ለቀው እንዲወጡም ሰሞኑን ማስጠንቀቂያ አስተላልፋለች።   ከ1,2 ሚሊዮን በላይ ሊባኖሳውያን እስካሁን ከቀያቸው መፈናቀላቸው ተሰምቷል።  የፈረንሳይ ዜና ምንጭ እንደዘገበው እስራኤል ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ የሂዝቦላህ ታጣቂዎች ላይ በከፈተችው ጥቃት ሳቢያ ሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት የሚገኙ ​​ትምህርት ቤቶች፣ ሆቴሎች እና መኖሪያ ቤቶች በተፈናቃዮች ተጣበዋል። አንዳንዶች እንደውም ጎዳና ላይ ተጠልለው ይገኛሉ። በስልክ ያነጋገርናት ኢትዮጵያዊት ቅድስት ለአራት ቀናት ያህል ጎዳና ላይ ነበርን ብላለች። « ዳውራ ፤ዳውን ታውን የሚባል ቦታ ለአራት ቀናት ያህል ሜዳ ላይ ነበርን። አሁን ሀበሾች ብር አዋጥተው የቤት ኪራይ ከፍለውልን ጀበል የሚባል ቦታ ነው ያለነው።»

ለአራት ቀናት ጎዳና ላይ ያደሩት ኢትዮጵያውያን

ቅድስት እንደነገረችን ከእሷ ጋር በጠቅላላው አራት ሴቶች ፣ አራት ወንዶች እና ሁለት ህፃናት በጎ ፍቃደኛ ኢትዮጵያውያን የተከራዮላቸው ቤት ውስጥ ይገኛሉ።  ሁሉም በአንድ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ቢሆንም ለመጠራራት እንኳን ጊዜ አላገኙም ነበር።  «እንደ አጋጣሚ ሆኖ ግን ነፍሴ አውጪን ብለን ሁላችንም ወደ ውጪ ስንሮጥ» ጎዳና ላይ ተገናኝተን ሽሽት ጀመርን » ስትል ቅድስት ተናግራለች። «ሌሊት 9 ሰዓት ተኩል ላይ ነው ጥቃት የተጀመረው። በዛን ሰዓት መስኮቱ፣ ሁሉ ነገር ሲገነጣጠልብን አምልጠን ወጣን። ልብስ አላልን፣ ምንም አላይዝንም። ከዛ ጎዳና ላይ፣የልጆች መጫወቻ ቦታ ተቀመጥን። አንዳንድ ሰዎች አንሶላ የመሳሰሉት እየሰጡን አንጥፈን መቀመጥ ጀመርን። ከዛ በኋላ በጎ አድራጊዎች እየመጡ ልብስ ፣ የምንጠቀምባቸው ሞዴስ እና ፓንት ይረዱን ጀመር። ከዛ ዝናብ ሊዘንብ ሲል ሰላም የምትባል አስተባብራልን ወደዚህ ቤት አመጣችን።»

 ከእስራኤል የአየር ድብደባ በኋላ በቤይሩት ደቡባዊ ሰፈር ጭስ ወደላይ ሲወጣ
ከእስራኤል የአየር ድብደባ በኋላ በቤይሩት ደቡባዊ ሰፈርምስል Hassan Ammar/AP/picture alliance

ሌላዋ ተፈናቃይ ኢትዮጵያዊት ቲና ትባላለች። በጦርነቱ ምክንያት ከምትኖርበት ቦታ ተፈናቅላ እሷም ጎዳና ላይ ከቆየች በኋላ ነዉ መጠለያ ያገኘችው። «እኔም የምኖርባት ቦታ ተመቷል። ከዛ ምንም ልብስም፣ ጨርቅም ሳልል ነው የወጣሁት። እኔ አሁን ያረፍኩት ጓደኛዬ ጋር ነው። እዚህ አንድ አምስት ሰዎች ተጠልለናል።»
ዳህዬ በደቡባዊ ቤሩት ጫፍ ላይ የምትገኝ ከተማ ስትሆን በዚህ አካባቢ 20, 000 የሚደርሱ የፍልስጤም ስደተኞች ይገኛሉ። ቦታውም በአብዛኛው የሱኒ ሙስሊሞች የሚኖሩበት ነው። ሌልሳ ከዚህ ቦታ ነው የተፈናቀለችው።  የምትኖርበት ቤት መስኮት ረግፏል። ለ1 ሰዓት ተኩል ያህል ከእነቅድስት ጋር በሌሊት በእግሯ ተጉዟ ነው ያመለጠችው። «እኔ ከልጄ ጋር ነበርኩ። የስምንት ወር ልጅ አለኝ። እኛ አካባቢ እንዳለ ቤቶች ፈርሰው ወጣሁ። ጓደኛዬ ናት የቀሰቀሰችኝ። ሌሊት ነበር። በጣም ከባድ ነበር»
ቅድስት ከሌልሳ እና ሌሎች ተፈናቃዮች ጋር ለአራት ቀናት ጎዳና ላይ በቆየችበት ሰዓት የባንግላድሽ እና የሶርያ ዜጎች እዛው ጎዳና ላይ እንደነበሩ አይታለች። ኢትዮጵያዊትዋ ወጣት ሊባኖስ ውስጥ ህጋዊ ሰነድ የላትም። «በቤት ሰራተኝነት ማዳም ቤት ተቀጥሬ እሰራ ነበር።» የምትለው ቅድስት አሁን ላይ ከዛ ጠፍታ ሌላ ቦታ ፅዳት እና መስተንግዶ እየሰራች ነበር። አንዴ ከሊባኖስ ከወጣች መመለስ እንደማትችል ታውቀዋለች። ስለሆነም ለቆ መውጣት የማታስበው ነገር ነው። «እኛ ተኝተን አናውቅም አንድ ሁለት ወር ሆኖናል። ይኼ ጦርነት ይጀመራል ከተባለ ጊዜ አንስቶ ተኝተን አናውቅም። ገጠሩ አካባቢ ይኼ ጦርነት ከተጀመረ አንድ አራት ወር ሆኖታል። ወደ እኛ ግን አልመጡም ነበር። አሁን ጦርነቱ ከተማ ገብቷል።»

«ሜዳ ላይ አልጥላቸውም»

የቲና ጓደኛ ሃና ትባላለች። ውጊያ ከተካሄዱባቸው አካባቢዎች የተሰደዱ ጓደኞቿን በአሁኑ ሰዓት ቤቷ አስጠልላለች። «ያው ጓደኞቼ ናቸው። በዛ ላይ ቤታቸው ስለፈረሰ ሜዳ ላይ አልጥላቸውም። ነገሮች እስከሚረጋጉ ድረስ ያለውን በልተን እንጠጣለን ብዬ ወደ እኔ ጋ ያመጣኃቸው። ያለሁት ቤሩት ውስጥ የክርስትያን አካባቢ ነው። እስካሁን እኛ ጋር ምንም ነገር የለም»

ከእስራኤል ጥቃት በኋላ ሊባኖስ ውስጥ ጎዳና ላይ የተፈናቀሉ ተኝተው
ከ 1,2 ሚሊዮን በላይ ሊባኖሳውያን ተፈናቅለዋልምስል Getty Images

ቤይሩት የምትኖረው ሰላማዊት ተስፋዬ ወይም ብዙዎች በሚያውቋት መጠሪያ ሰላም፤ የፍካት ለኢትዮጵያ ማህበር አባል ናት። ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ጋር ግንኙነት ስላላት ከዚህ ቀደምም በዚሁ ዝግጅት ኢትዮጵያውያን ስለሚገኙበት ሁኔታ ጠይቀናት ነበር።  ሁኔታዎች አሁን ላይ ይበልጥ እየከበዱ መጥተዋል ትላለች።  ሰላም ቀደም ሲል የሰማችኋቸው ኢትዮጵያውያን ከጎዳና እንዲነሱ ያመቻቸች ወጣት ናት። 
«እግዚአብሔር ይመስገን። እኛ ጎዳና ላይ አለን ብዬ የምለው የለም። እየተናበብን ተቀኛጅተን እየሰራን ህዝቡን ከመንገድ እያነሳን ነው። በየፅህፈት ቤቱ እና እህቶቻችን ቤት እያስቀመጥን ችግሩን ለመቅረፍ ስራዎች እንዲሰሩ ርብርብ እያደረግን እንገኛለን። «ጦርነቱ አይደለም የውጭ ሀገር ዜጎችን ራሱ ሊባኖሲያውያን ሳይቀሩ ሰላም እና መረጋጋት ወደሌለባት ሶርያ እንዲሰደዱ ያደረገበት ሁኔታ ነው ያለው » የምትለው ሰላማዊት ወይም ሰላም በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሊባኖስ ውስጥ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉም ጠይቀናታል።

ከእስራኤል ጥቃት በኋላ በህንፃዎች ላይ የደረሰ ጉዳት
ከእስራኤል ጥቃት በኋላ በህንፃዎች ላይ የደረሰ ጉዳትምስል Hussein Malla/AP/picture alliance

ኢትዮጵያውያን በምን ሁኔታ ላይ ናቸው?

«ከቤተሰብ እና አሰሪዎቻቸው ጋር ለቀው የወጡ አሉ። እኛ ግን መጠለያ አጥተው ከተቀበልናቸው ሳምንት እያስቆጠርን ነው። ያ ማለት ደግሞ  ሁሉም ሊባኖስ ውስጥ ያለ ኢትዮጵያዊ ችግር ውስጥ ነው። መራብ መጠማት አይደለም። ወደ ሀገሩ መሄድ ይፈልጋል። ያንን ነገር ደግሞ ለማድረግ አንደኛ በረራ ዝግ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ሰነድ አልባዎች ይበዛሉ። »
ቤይሩት የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ፅህፈት ቤት ሊባኖስ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የምዝገባ ጥሪ እያደረገ ነው። በፌስ ቡክ ገፁ ሰሞኑን በአጋራቸው መረጃዎች መሠረት በጦርነቱ ምክንያት ከሊባኖስ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን እንዲመዘገቡ ያሳስባል። ዜጎችም ከሊባኖስ እንዲወጡ የሚችሉበት መንገድ ከሊባኖስ ኢሚግሬሽን ጋር ለማመቻቸት እየተሰራ እንደሆነ ጠቁሟል።  « እኛም አብረናቸው እየሰራን ነው። እንደውም አሁን የሰው ኃይል ያስፈልጋል ተብሎ አብረናቸው እየሰራን ነው።» የምትለው ሰላም « መመዝገብ የሚፈልጉ ፣ የቆዮ ፣ ወረቀት የሌላቸውን እየመዘገብን እንገኛለን። ይኼ ደግሞ ተዘጋጅቶ ለመቆየት ነው እንጂ መሬት የወረደ ነገር የለም። ግን ደግሞ ምዝገባ መጀመሩ ለህዝቡም  ሆነ ለእኛ አንድ ተስፋ ነው። የቆንስላ ፅህፈት ቤት ስድስት ስልክ ቁጥሮች ለቋል። ግን የፅህፈት ቤቱ ሰራተኞች ሌሎች ስራዎችም ስለሚገጥማቸው ምዝገባው ላይ ብቻ ማተኮር አልቻሉም። ስለሆነም የሰው ኃይል ያስፈልገናል ብለው ጠይቀውን ነው በበጎ ፍቃደኝነት ይህን የማደርገው። »

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ