1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አቤቱታ

ረቡዕ፣ ሰኔ 26 2011

ሊባኖስ ውስጥ በስደት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን  ከሚደርስባቸው ችግር እና ስቃይ የሚታደጋቸው የመንግሥት አካል እንደሚያስፈልግ ተገለጸ። በጥቅሉ በአረብ ሃገራት የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለመብት ረገጣ እና የጉልበት ብዝበዛ መዳረጋቸው ቢነገርም  አሁንም መፍትሄ አላገኘም።

https://p.dw.com/p/3LX3R
Äthiopische Hausangestellte im Libanon
ምስል picture-alliance/AP Photo/G. Kassab

በሊባኖስ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ጥሪ

ከሳውዲ እስከ ኢምሬት፤  ከኩዌት እስከ ቀጠር፤ ከሊባኖስ እስከ ባህሬን ኢትዮጵያውያን  ላባቸውን አፍስሰው የሚያገኙትን ደመወዝ ከመነጠቅ ጀምሮ ሕይዎታቸውን  አደጋ ላይ የሚጠል ፈርጀ ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀምባቸው ነው የሚነገረው። ይህ የመብት ጥሰት በተለይ ደግሞ ሊባኖስ በሚገኙት ዜጎች ላይ በመጥናቱ የአረብ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ በሰፊው እንደሚዘግቡት ነው ከጄዳ ነብዩ ሲራክ የላከልን ዘገባ የሚያስረዳው። እንደዘገባው በተለይ ሊባኖስ የሚታየውን የመብት ረገጣ የከፋ የሚያደርገው በቤሩት የቆንስል መሥሪያ ቤቱ ለዜጎች አቤቱታ ትኩረት ባለመስጠቱ ነው የሚል ወቀሳ ይሰማል። ከዚህም ሌላ በረቀቀ የሙስና መንገድ የታገደውን የጉብኝት ቪዛ እገዳ በመጣስ ወደ ሊባኖስ ዜጎችን በሕገወጥ የሚያሸጋግሩ ደላሎች ያመጧቸውን ኢትዮጵያውያን ለችግር እንደዳረጓቸውም ዘገባው አመልክቷል። ዜጎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት አስመልክቶ በሊባኖስ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ  ባወጣው ማሳሰቢያ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ጠይቋል። ነብዩ ሲራክ ዝርዝሩን ልኮልናል።

ነብዩ ሲራክ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ