1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጎርፍ አደጋ በሊቢያ፤ የአደጋዉን መጠን መቀነስ ይቻል ነበር?

ቅዳሜ፣ መስከረም 5 2016

በሊቢያ የባህር ወደብ ከተማ ደርና በደረሰዉ የጎርፍ አደጋ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ እና በ100 ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መኖርያ ቤቶቻቸዉን እንዳጡ ተነግሯል። የደርና ከተማ ነዋሪ ከሆነዉ አንድ ሦስተኛ ያህሉ አንድም በጎርፍ ታጥቦ ህይወቱን አጥቷል፤ አልያም የደረሰበት አይታወቅም። የሟቾች ቁጥር 20 ሺህ ሳይደርስ አይቀርም ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4WPOJ
በአንድ ወቅት 100,000 ገደማ ነዋሪዎች የነበሩባት ደርና ከተማ ከአደጋዉ በኃላ አንድ አራተኛ የሚሆነው ሕዝብ ጠፍቷል ወይም ሞቷል የሚል ስጋት አለ።
በአንድ ወቅት 100,000 ገደማ ነዋሪዎች የነበሩባት ደርና ከተማ ከአደጋዉ በኃላ አንድ አራተኛ የሚሆነው ሕዝብ ጠፍቷል ወይም ሞቷል የሚል ስጋት አለ።ምስል AFP

"የአየር ፀባይ መቆጣጠርያ እና የአደጋ ጊዜ መከላከያ ቢኖር ኖሮ ነዋሪችንም በሰዓቱ ማስጠንቀቅ እና ከአካባቢዉ ማስወጣት በተቻለ ነበር።"

ከስድስት ቀናት በፊት በሊቢያ የባህር ወደብ ከተማ በሆነችዉ ደርና በደረሰዉ የጎርፍ አደጋ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ እና በ100 ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መኖርያ ቤቶቻቸዉን እንዳጡ ተነግሯል። ከአካባቢዉ በሚወጡ መረጃዎች መሰረት የደርና ከተማ ነዋሪ ከሆነዉ አንድ ሦስተኛ ያህሉ አንድም በጎርፍ ታጥቦ ህይወቱን አጥቷል፤ አልያም የደረሰበት አይታወቅም። የዓለም የቀይ ጨረቃ ማኅበር ትናንት አርብ እንደገለፀዉ የሟቾች ቁጥር  11 ሺህ 300 ደርሷል። ቁጥሩ ሊጨምር በልጥ ይችላል። በጎርፍ የታጠበችዉ የደርና ከተማ ከንቲባ በበኩላቸዉ 20 ሺህ ሰዎች ሞተዋል ሲሉ ተናግረዋል። ነዋሪዎች የዘመዶቻቸዉን አስክሬን ደለልን እየቆፈሩ እየፈለጉ ነዉ። በጎርፉ ታጥበዉ እስከ 100 ኪሎሜትር ድረስ የተወሰዱ ሰዎች አስክሬንም እየተገኘ መሆኑ ተነግሯል። ዳንኤል የተባለ ዝናብ የቀላቀ አዉሎንፋስ፤ ባስከተለዉ ሱናሚ መሰል ጎርፍ ሦስት ግድቦችን አፍርሶ የባህር ዳርቻዋን የሊቢያን ደርና ከተማን በኃይለኛ ጎርፍ አጥቦ አዉድሟል። በነዳጅ ዘይት የበለፀገችዉ ሊቢያ በተፈጥሮ አደጋ በርካታ ሕዝብ ሲያልቅባት በተመዘገበ ታሪኳ ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ። የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊና የአስቸኳይ ርዳታ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሐፊ ማርቲን ግሪፊቲስ እንዳሉት አደጋዉ የአየር ንብረት መዛባት ዉጤት ነዉ። ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰዉ ደግሞ አደጋን ለመከላከልና ከደረሰ በኋላም ሰዎችን ለመርዳት በቅጡ የሚያስተባብር ኃይል ባለመኖሩ ነዉ። አንድ ከጎርፍ አደጋ የተረፈ የደርና ከተማ ነዋሪ ያየዉን እንዲህ ይናገራል።

በሰሜናዊ ሊቢያ ከተደረመሱ በኃላ አውዳሚ የጎርፍ መጥለቅለቅ ከተከሰተ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል ሌሎች ብዙዎች የደረሱበት አይታወቅም።
በሰሜናዊ ሊቢያ ከተደረመሱ በኃላ አውዳሚ የጎርፍ መጥለቅለቅ ከተከሰተ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል ሌሎች ብዙዎች የደረሱበት አይታወቅም።ምስል Esam Omran Al-Fetori/REUTERS

«ለሊት ከፍተኛ የፍንዳታ አይነት ድምፅ ቀሰቀሰን። ደርና የሚኖር ሁሉ በእርግጠኝነት ይህን የፍንዳታ ድምፅ ሰምተዋል። እየጋለበ ከተማዉን ያጥለቀለቀዉን ዉኃ አኳኻን መግለጽ በጣም ከባድ ነዉ። የዉኃዉ ግስጋሴ ድምፅ ሁሉ ይሰማዉ ነበር። ከቤታችን ከቤት ወጥተን ስናይ ከተማዋ በጎርፉ ታጥባ ከተማ የሚባል ነገር አልነበር። ሁሉ ነገር ወድሟል። የጎርፉ ዉኃ በሰዉ ቁመት ልክ ነበር። » 

በጎርፍ ታጥበዉ የተወሰዱ ሰዎች አስክሬን፤ በቤታቸዉ በዉኃ ታፍነዉ የሞቱ ሰዎች አስክሪን በበጎ ፈቃደኞች በላስቲክ ከረቲጥ እየተሰበሰበ ጎርፍ በፈራረሰዉ እና በደለል እና በጭቃ በተሞላዉ የደርና ከተማ ጎዳና ላይ ተደርድሮ ለጅምላ ቀብር እየተዘጋጀ ይታያል።  በርካታ ከጎርፉ የተረፉ የደርና ነዋሪዎች ግድቡ እስኪፈነዳ ድረስ በአደጋ ዉስጥ ስለመኖራቸዉ የሚያዉቁት ነገር እንደሌለ እንዲህ ተናግረዋል። 

የጀርመን የቴክኒክ እርዳታ ድርጅት ሰራተኞች ወደ ሊቢያ ጀነሬተሮችን ለማጓጓዝ በዝግጅት ላይ
የጀርመን የቴክኒክ እርዳታ ድርጅት ሰራተኞች ወደ ሊቢያ ጀነሬተሮችን ለማጓጓዝ በዝግጅት ላይምስል Stefan Puchner/dpa

«አሁንም ከፍርስ ራሽ ቤቶች እና በዉኃ ከተሞሉ ቤቶች ዉስጥ አስክሬን እየቆፈርን እያወጣን ነዉ።  »

የሊቢያዉ መሪ ሞአመር ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ ከዛሬ 12 ዓመት በኃላ ሊቢያ ለዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ተዘፍቃ፤ የተቀናቃኝ ቡድኖች እና የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች እና ዘራፊዎች መነሃርያ ሆናለች። ሀገሪቱ የስደተኛ አሸጋጋሪዎች ገንዘብ ማግኛ የስደተኞች ማሰቃያ ቦታ በመሆንዋ ትታወቃለች። በመዲናዋ ትሪፖሊ የሚገኘዉ እና በዓለም አቀፍ እዉቅና የተሰጠዉ የሊቢያ መንግሥት ዳንኤል በተባለዉ አዉሎንፋስ እና ዝናብ ባስከተለዉ ሱናሚ መሰል ጎርፍ የወደመዉ ደርና የባህርዳርቻ ከተማን ጨምሮ የሊቢያን ምስራቃዊ ክልል የሚቆጣጠር ነዉ። "ይህ አደጋ የተፈጥሮ አደጋ ብሎም ሰው ሠራሽ አደጋ ነው ሲሉ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የሊቢያ የደኅንነት ጉዳይ ተንታኝ አያ ቡርዌላ አዉሎንፋስ የቀላቀለ ዝናብ ያስከተለዉ ከባድ ጎርፍ የተፈጥሮ አደጋ ቢሆንም፤ ከዚያ በኋላ ያየነው መዘዝ ግን ሰው ሠራሽ ነዉ ብለዋል። አያ ቡርዌላ እንደገለጹት በሊቢያ በመሠረተ ልማት ላይ አልተሰራም፣ በሀገሪቱ ተስፋፍቶ በሚታየዉ ሙስናን ጨምሮ  ደርናን የመታው ጎርፍ " ከባድ አደጋ እንዲያስከትል  ምክንያት ሆነዋል ሲሉ ተናግረዋል።  የዓለም የሜትሮሎጂ ጉዳይ ድርጅትም በሊቢያ ለዓመታት የዘለቀዉ የእርስ በእርስ ጦርነት እና መከፋፈል በሃገሪቱ በአግባቡ የሚሠራ የአየር ትምበያ አገልግሎት እንዳይገነባ አድርጓል፤ የትንበያ መሳርያ ቢኖር ኖሮ ይህ አደጋ ሳይደርስ መታደግ ይቻል ነበር ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

በጎርፍ የታጠበችዉ የደርና ከተማ ከንቲባ  20 ሺህ ሰዎች ሞተዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በጎርፍ የታጠበችዉ የደርና ከተማ ከንቲባ 20 ሺህ ሰዎች ሞተዋል ሲሉ ተናግረዋል።ምስል Esam Omran Al-Fetor/REUTERS

«የአየር ፀባይ መቆጣጠርያ እና የአደጋ ጊዜ መከላከያ ቢኖር ኖሮ ይህ ሁሉ ነገር ባልተከሰተ ነበር።  ነዋሪችንም በሰዓቱ ማስጠንቀቅ እና ከአካባቢዉ ማስወጣት በተቻለ ነበር። በእርግጥ የኢኮኖሚ ዉድመቱን  መቅርፍ ባይቻልም ቦታዉ ላይ ትክክለኛ የማስጠንቀቅያ መሳርያ ቢኖር ኖሮ  የሟቾች ቁጥርን መቀነስ አይገድም ነበር። »   

ጀርመን እና ፈረንሳይን ጨምሮ የዓለሙ መንግሥታት፤  መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በጎ ፈቃደኞች በሰሜን ምስራቅ ሊቢያ ደርና ላይ እርዳታ መስጠት ጀምረዋል።

በሊቢያ ከባድ የጎርፍ አደጋ ከተከሰተ በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የገለፀዉ የተባበሩት መንግስታት የአደጋ ጊዜ ቢሮ  ለ 250,000 ሊቢያውያንን 71.4 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ጠይቋል።

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ