1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

«ለይምሰል ሳይሆን የምወደው ሥራ ነው»

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 1 2014

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዳችን የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህር ነው። ወጣቱ መምህር በትርፍ ጊዜው ደግሞ የተወሰኑ ልጆችን እቤት ድረስ እየሄደ እስከ ማታ ድረስ ያስጠናል። ለምን ቋንቋ ማስተማር እንደሚያስደስተው እና ተማሪዎቹን እንዴት ዕውቀት እንደሚያስገበያቸው ገልጾልናል።

https://p.dw.com/p/4443g
Äthiopien | Birhanu Fekade
ምስል privat

እንግሊዘኛ ቋንቋ ለብርሃኑ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ በርካታ የእንግሊዘኛ መምህርራን  አፉን የፈታበት ቋንቋ አይደለም። ነገር ግን ከልጅነቱ አንስቶ ለቋንቋው ፍቅር እንደነበረው እና ቤተሰቦቹም ቋንቋውን እንዲችል ይደግፉት እንደነበር ይናገራል።  «ታላላቅ ወንድሞቼ እና እናቴ በጣም ድጋፍ ያደርጉልኝ ነበር። እናቴም ትንሽ ትንሽ እንግሊዘኛ ትችላለች እና በእንግሊዘኛ ሳወራት ታበረታታኝ ነበር። » ይላል።  ትምህርት ቤት ክፍል ውስጥ ሲገባ ከተማሪዎቹ ጋር «ሙሉ በሙሉ በእንግሊዘኛ ቋንቋ አናወራም። መተርጎም ያለበት ቦታ እተረጉምላቸዋለሁ » የሚለው ብርሃኑ ከእንግሊዘኛ ባልደረቦቹ ጋር ደግሞ ብዙውን ጊዜ በእንግሊዘኛ ለመግባባት እንደሚሞክሩ ገልፆልናል።  አንድን ቋንቋ ለመቻል ልምምድ ያስፈልጋል። ያኔ ደግሞ ስህተት መስራት የተለመደ ነው። ይሁንና በተለይ ትምህርት ቤት አካባቢ ያሉ ተማሪዎች ስህተት ላለመስራት ሲሉ መናገሩን አይደፍሩም። ይህ ትልቁ የቋንቋ መምህራን ፈተና ነው። ብርሃኑ እንደታዘበው « ሲሳሳቱ ጓደኞቻቸው ይስቁብናል ብለው የሚያፍሩ አሉ። የቤተሰብም ተፅዕኖ ያለባቸው አሉ።» ስለሆነም ያንን ችግር እንዲረሱ አበረታታቸዋለሁ ይላል።
ብርሃኑ ከዋና ስራው በተጨማሪ አዲስ አበባ ውስጥ እየተዘዋወረ ተማሪዎችን በትርፍ ጊዜው ያስጠናል። « ሁለት ቦታ የማስጠናቸው ልጆች አሉ።»  ይህንን ስራ ሲሰራ ደግሞ እስከ ማታ ድረስ አምሽቶ ይሰራል። «መምህር መሆን ዜጋ መቅረፅ ነው።» የሚለው ብርሃኑ በስራው ደስተኛ ነው። ይሁንና እድሜ ልኩን መምህር ሆኖ የመቀጠል አላማ የለውም። ወደፊት የሚፈልገውን ግን ገና አልወሰነም። «በቅርቡ የሁለተኛ ዲግሪዬን ስጨርስ» እወስናለሁ ብሎናል።  ከኢትዮጵያ አስተያየት እንደሚልኩን በርካታ መምህራን ከሆነ መምህራኑ ለሚያበረክቱት ስራ ተገቢ የሆነ ክፍያ አያገኙም። ይህም ስራቸውን ለመቀየር ከሚገደዱበት ምክንያቶች አንዱ ነው። « የምንሰራው ስራ እና የmmik,ፈለው ክፍያ ብዙ ጊዜ አይመጣጠንም ግን እንደዛም ሆኖ ስራው ያስደስታል። አሁን ለይምሰል አይደለም የምናገረው በስራዬ ደስተኛ ነኝ።»ይላል ላለፉት ስድስት ዓመታት የእንግሊዘኛ ቋንቋ መምህር ሆኖ የሚያገለግለው ብርሃኑ ፈቃደ።

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ