ለኢትዮጵያ ሰላም የዩናይትድ ስቴትስ ጥሪ
ሐሙስ፣ የካቲት 14 2016የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እና የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ትናንት በበይነ መረብ በጋራ በሰጡት መግለጫ መንግሥት ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ለዳግም ውይይት እንዲቀመጥ አሜሪካ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ድጋፍ እንደምታደርግም ገልፀዋል። ሁለቱ ባለሥልጣናት የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆንም አሜሪካ ድጋፏን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ማይክ ሐመር ስለ ኢትዮጵያ ግጭት ምን አሉ ?
ኢትዮጵያ ውስጥ በተጋጋሚ እየተገኙ ከሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት እያደረጉ ያሉት ዩናይትድ ስቴትስየአፍሪካቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ባለፈው ሳምንትም አዲስ አበባ እና መቀሌ ተገኝተው በኢትዮጵያ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል። ትናንት ከሀገራቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ጋር በበይነ መረብ በጋራ በሰጡት መግለጫ መንግሥት ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር ዳግም መነጋገር ከፈለገ ለመመቻቸት፣ ከፋኖ ጋር ለመወያየት የሚችልበት ዕድል ካለ በደስታ እንደምትቀበል የመንግሥታቸውን አቋም መግለፃቸውን ተናግረዋል።
«ባለፈው ኅዳር በዳሬሰላም ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋር በተደረገው ድርድር በቀጥታ ተሳትፈናል። ለሁለቱም ወገኖች ባቀረብነው ጥሪ መሰረት ለዚያ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔን ለማመቻቸት ዝግጁ ነን። ከፋኖ ጋር የመገናኘት ዕድል ካለም፣ ሰላምን ለማስፈን የምንሞክርበትን ዕድል በደስታ እንቀበላለን። በተደጋጋሚ እንደተናገርነው ለእነዚህ ግጭቶች ከዉጊያ መፍትሔ አይኖርም። እንደ እውነቱ ከሆነ አሁን ትኩረት መደረግ ያለበት ስለ ውይይት እንዲሁም በእርግጥም የዜጎችን ጥበቃ በማረጋገጥ ላይ ነው።»
ዐቢይ ግጭቶችን በሰላም እንደሚፈቱ ነግረውናል - ሞሊ ፊ
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉትና ከማይክል ሀመር ጋር ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከተለየ ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት ነግረውናል ያሉትንም አቋም አብራርተዋል።
«ብዙ የመንግሥት አካላትን እንዲሁም የማኅበረሰብ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን አግኝተናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እያጋጠሟት ያለውን ፈተና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ ነኝ ብለዋል። በዚህ ቁርጠኝነት ላይ ጠንክረው እንዲሠሩ እናበረታታለን። የፀጥታ አካላት ለሚኑሱ ተቃውሞዎችም ሆነ ጥቃቶች ምላሽ በሚሰጡበት ጊዜ የሚወስዱት እርምጃ የሚያሳስበን መሆኑን በይፋም በግልም ገልጸናል። የተወሳሰበ የደህንነት ፈተና እንደሆነ እናውቃለን፣ ነገር ግን የሲቪሎችን መብት ለማክበር ብዙ መደረግ አለበት። የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሁለቱም ክልሎች መረጋጋት እንዲሰፍን በሚያደርጉት ጥረት በየክልሉ ባሉ አምባሳደሮቻችን በኩል ቆመናል።»
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ «ለአማራ ክልል ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበናል። እንነጋገር፣ እንወያይ፣ እንታረቅ፣ እንስማማ» ሲሉ ሰሞኑን በጽሕፈት ቤታቸው ላወያዩዋቸው ሰዎች ገልፀዋል። አምባሳደር ማይክል ሀመር ይህንኑ ሀሳብ በመግለጫቸው አራምደዋል። «የኢትዮጵያ መንግሥት ለውይይት ክፍት መሆኑን መግለጹን እናደንቃለን። በአማራ እና በኦሮሚያ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ በተመለከተም ሥጋታችንን አንስተን መንግሥት የዜጎችን ጥበቃና ከለላ እንዲያረጋግጥ እንዲሁም ወንጀለኞችን በሕግ እንዲጠየቅ አሳስበናል።»
የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ
አምባሳደር ማይክል ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የሽግግር ፍትሕ እና የብሔራዊ ውይይት አስፈላጊነት በአጽንኦት ያነሱ ሲሆን ያለፉ ቅሬታዎችን ለማስወገድ እና ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ አቅጣጫ ለማራመድ ቁልፍ መሆናቸውን ገልፀዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ የ15 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ አሁንም ጥሪ እያደረገች መሆኑ እና ስምምነቱ ከተፈረመ ከ 15 ወራት በኃሏ ሁለቱ የስምምነቱ ፈራሚዎች አሁንም ለሰላም ቁርጠ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ በግጭቱ ተሳታፊዎች ላይ ማዕቀብ ትጥል ይሆን ?
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ያደርጉት የነበረውን ጦርነት ባየበት ዐይን ይመለከት እንደሆን፣ ግጭቱን በሰላም ለመፍታት ፈቃደኛ ባልሆኑ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ይጥል እንደሆን፣ በሁለቱ ትልልቅ ክልሎች ከባድ ግጭት እየቀጠለ ቢሆንም የአሜሪካ ባለሥልጣናት ጉዳዩን በአግባቡ ትኩረት ስለመስጠት አለመስጠታቸው የተጠየቁት ሞሊ ፊ ቀጥተኛ ምላሽ ሳይሰጡበት ቀርተዋል።
በሁለቱ ባለሥልጣናት መግለጫ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ. ም በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ በኩል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ውጥረት ማስከተሉን ፣ ከሁለቱ ሃገራት መሪዎች ጋር በተናጠል መወያየታቸውን ሞሊ ተናግረዋል። ጉዳዩ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት በማክበር ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ውጥረቱ እንዲረግብ ማሳሰባቸውንና የኢትዮጵያን የንግድ ማሳለጫ የባሕር በር የማግኘትን ጉዳይ «ተገቢ አሳሳቢ ጉዳይ» መሆኑንም ገልፀዋል። ጉዳዩ በሶማሊያ እና በሶማሊላንድ ሕዝብ እንጂ በውጭ ተዋናዮች መፈታት እንደሌለበት ፤ ያ ካልሆነ በቀጣናው የበለጠ ግጭት ሊፈጥር እንደሚችልም አብራርተዋል።
ሰለሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ