1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"የፌድራል መንግሥት የበጀት ድጎማ ማድረግ አይችልም" የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ

ቅዳሜ፣ መስከረም 30 2013

ከትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ዶክተር ደብረጺዮን ከሚመሩት ሥራ አስፈፃሚ የፌድራል መንግሥት ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥ የወሰነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀት እንዲቋረጥ መወሰኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/3jZZV
Äthiopien l Adem Farah, Sprecher House of Federation
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህምስል Ethiopia House of Federation

የትግራይ ክልል ከፌድራል መንግሥቱ የሚመደብለት የድጎማ በጀት  እንዲቋረጥ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ወሰነ። የውሳኔው መሠረት የትግራይ ገዢ ፓርቲ እና ክልላዊ መንግሥት የፌደሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔን በመቃወም ትግራይ ዉስጥ ባለፈው ጳጉሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.  ምርጫ በማድረግ የተመሠረተዉ የትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ሥራ አስፈፃሚ ካቢኔ "ሕገ-ወጥ" በመባሉ ነው። 
"የፌድራል መንግሥት ድጋፍ መስጠት የሚችለው ለሕጋዊ አካል ነው። ከዚህ አኳያ የክልሉ ምክር ቤት እና የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካል ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ምርጫን ተከትሎ የተቋቋሙ ስለሆኑ ሕጋዊ አይደሉም። ስለሆነም ማንኛውም የፌድራል ተቋም ከእነዚህ አካላት ጋር ግንኙነት ማድረግ ስለማይችል ለእነዚህ አካላት የፌድራል መንግሥት የበጀት ድጎማ ማድረግ አይችልም" ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ መንግስት ለሚቆጣጠረዉ የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል። 

ምክር ቤቱ በትናንትናው ዕለት የፌድራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ከሥራ አስፈፃሚው ጋር ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥ ወስኖ ነበር። ምክር ቤቱ ትናንት መስከረም 26 ስብሰባ አድርጎ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት  የፌድራል መንግሥት "የወረዳ፣የከተማና የቀበሌ አስተዳደሮችን ጨምሮ በክልሉ ከሚገኙ ህጋዊ ተቋማት ጋር ብቻ የሥራ ግንኙነት ማድረግ አለበት።" 
የፌድራል መንግስት «ሕገ ወጥ» ባለው ምርጫ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ አሸንፎ ባለፈው መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም የትግራይ ክልል ምክር ቤት የተቋቋመ ሲሆን ክልሉን ላለፉት ሁለት ዓመታት በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ የቆዩት የህወሓት ሊቀ-መንበር  ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ርዕሰ-መስተዳድር ሆነው ተሹመዋል። 

Äthiopien Politiker Debretsion Gebremichael
የፌድራል መንግስት «ሕገ ወጥ» ባለው ምርጫ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ አሸንፎ ባለፈው መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ተመስርቷልምስል Million Hailesilassie/DW

የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ከመስከረም 25 በኋላ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የጠቅላይ ምኒስትሩ ሥልጣኖች ሕጋዊ አይሆኑም ሲሉ ባለፈው ባለፈው መስከረም 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ለትግራይ ብዙኃን መገናኛ ኤጀንሲ ተናግረዋል። 

አቶ አስመላሽ የጠቀሷቸው ሥልጣኖች በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫ ባለመካሔዱ ምክንያት ሕገ-መንግሥት ተተርጉሞ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የተራዘሙ ናቸዉ። የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ግን ይኸን አይቀበሉም። አቶ አስመላሽ ከመስከረም 25 በኋላ "ይኸ መንግሥት ሕጋዊ ስላልሆነ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በምኒስትሮች ምክር ቤት፣ በጠቅላይ ምኒስትር የሚሰጡ ትዕዛዞች እና ውሳኔዎች የሚወጡ ሕጎች ትግራይ ላይ ተቀባይነት የላቸውም" ብለው ነበር።  

የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ህወሓት በፌድራል መንግሥቱ ለተሾሙ አስራ ሶስት አባላቱ "ኃላፊነታችሁን በማቆም ለድርጅታችሁ ሪፓርት እንድታደርጉ" የሚል ትዕዛዝ አስተላልፏል። ትዕዛዙ ከተሰጣቸው መካከል የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካሪ እና ከህወሓት ነባር ታጋዮች አንዱ የሆኑት አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር)፤ የቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አባይ ወልዱ እና አምባሳደር አዲስአለም ባሌማ ይገኙበታል። 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ