1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች

ዓርብ፣ ሚያዝያ 8 2013

እግር ኳስ በዓለማችን ላይ እጅግ ተወዳጅ እና በስፋት ከተዘወተሩ የቡድን ጨዋታዎች አንዱ ነው። እግር ኳስ  ማኅበራዊ አንድነትን የሚፈጥር ጨዋታም ነው።ለመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ማለት ምን አይነት ስሜት ይፈጥራል?

https://p.dw.com/p/3s6uI
Äthiopien Fußball Nationalmannschaft
ምስል ISSOUF SANOGO/AFP

የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች

እንደዛሬው በኮሮና ወረርሽኝ ጨዋታቶች ከመስተጓጎላቸው በፊት ከሁሉም የኑሮ ደረጃ የተውጣጡ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ስታዲዮም በመሰባሰብ ወይም በቴሌቪዥን መስኮት እና በራዲዮ ጨዋታዎችን እየተከታተሉ ለቡድናቸው ድጋፋቸውን ይገልፃሉ። ደጋፊዎቹም በሀገር እና በአኅጉር የተወሰኑ አይደለም። ለመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሔራዊ ቡድን መጫወት ማለት ምን አይነት ስሜት ይፈጥራል? «ብዙ ልዩነት አለው» ይላል ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የተቀላቀለው ሱራፌል ዳኛቸው። «ሁሉንም ክለብ እና ህዝብ ወክለን፣ ለአንድ ባንዲራ ነው የምንጫወተው። ስለዚህ ትልቅ ጫና እና ኃላፊነት ነው ያለው» የሚለው ሱራፌል ከብሔራዊ ቡድኑ ውጪ ለፋሲል ከነማ ስፖርት ቡድን ይጫወታል።

የ19 ዓመቷ መሳይ ተመስገን ደግሞ ለኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎች) እንድትጫወት ስትጠራ ባለፈው ሳምንት ደቡብ ሱዳንን 11 ለ 0 ያሸነፉበት የወዳጅነት ግጥሚያ የመጀመሪያዋ ነው። « በበመረጤ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ቡድኑን ስቀላቀልም ቡድኑ በታዳጊዎች የተደገፈ ነው። አሰልጣኞቻችንም ከጎናችን ነበሩ። ያግዙናል። »ሉሲዎች ደቡብ ሱዳንን በሰፊ ልዩነት ባሸነፉበት ጨዋታቸው  መሳይ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ነበረች። በተቻላት መጠንም ለአጥቂዎች ኳስ በማቀበል ለስኬታቸው የበኩሏን አስተዋፅዎ እንዳደረገች ታምናለች።

የ 24 ዓመቱ በረኛ ወይም ግብ ጠባቂ ተክለማሪያም ሻንቆ ከ2008 ዓ.ም አንስቶ በተደጋጋሚ ለብሔራዊ ቡድኑ እንዲጫወት ጥሪ ቢቀርብለትም በጨዋታ ሲሳተፍ የአሁኑ የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያው እንደሆነ ይናገራል።  « በወቅቱ ወጣት ስለነበርኩ እና ልምድ ያላቸው ጎል ጠባቂዎች ስለነበሩ እድሉን አላገኘሁም። አሁን ግን በቋሚነት ብሔራዊ ቡድኑን እያገለገልኩ እገኛለሁ» ይላል።

Äthiopien Sport l Frauenmannschaft U20
ከ 20 ዓመት በታች የሆኑ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ሲለማመዱምስል DW/O. Tadele

ሌላዋ አዲስ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የምስራች ሞገስ ትባላለች።  17 ዓመቷ ነው። « የደስታ ስሜት አለው፤ ከዛ ደግሞ  እንዴት ተመረጥኩ ብዬ ያለማመንም ነገር አለ» እና ስሜቱ ወደር የለውም ትላለች። የምስራች በሁለቱ የወዳጅነት ጨዋታዎች ኳስ ተከላካይ ሆና ለመጫወት ችላለች። የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ የምስራችም ትሁን ሌሎቹ ያነጋገርናቸው ወጣቶች ኳስ መጫወት የጀመሩት በልጅነታቸው ነው። የምስራች ዛሬ ህልሟን በማሳካቷ ብቻ ሳይሆን ደስተኛ የሆነችው፤ በተለይ እግር ኳስ የወንዶች ጨዋታ እንደሆነ ብቻ አድርገው የሚያምኑ የማኅበረሰቧን አመለካከት መለወጥ በመቻሏም ነው። « ሰፈር ውስጥ ወደቤት አትገቢም። ስራ አታግዥም ይሉኝ ነበር። ተወልጄ ያደኩት መርካቶ አካባቢ ነው። እና ይህ ተጽዕኖ እንዲጠፋ አድርጌያለሁ።»

መሳይ፤ እግር ኳስ መጫወት ማፍቀሯ እድል ብቻ ሳይሆን ብዙ ፈተናዎችን ይዞባት መጥቷል። የገጠማትን ፈተና ግን ለመግለፅ ዝርዝር ውስጥ ባትገባ ትመርጣለች። « ሁሉም ለሚወደው እግር ኳስ ዋጋ ከፍሏል።»  መሳይ መተሀራ ከተማ ነው ያደገችው።  ቀጣዩ የብሔራዊ ቡድን ግጥምያ መቼ እንደሆነ ዐታውቅም። በቅርቡ እንደሚሆን ግን ፍንጭ ተሰቶናል ትላለች። ከዚህ በፊት ለመብራት ኃይል እግር ኳስ ቡድን ነበር የምትጫወተው። አሁን ደግሞ ለመከላከያ ስፖርት ቡድን ትጫወታለች። ለብሔራዊ ቡድኑም የተመረጠችው እዛው ሳለች ነው።  ሉሲዎች ከደቡብ ሱዳን ጋር የነበራቸውን ግጥሚያ ያካሄዶት በኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ተመልካቾች ባልተሳተፉበት ነበር። ደጋፊ ባለመኖሩ የምስራች ብዙም ቅር አልተሰኘችም።የምስራች ብሔራዊ ቡድኑን የተቀላቀለችው እንደ ሌሎቹ ከቡድን ተመርጣ ሳይሆን በኢትዮጵያ ወጣቶች ማሰልጠኛ አማካኝነት ነው።  ወደፊትም ጥሩ ተስፋ ከሚጣልባቸው ሴት አዳጊ ተጫዋቶች አንዷ ናት።

ወደ ወንዶቹ የብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ስንመለስ ሱራፌልም እንደ ተክለማርያም 24 ዓመቱ ነው። ከሴቶቹ ተጫዋቾች ፈተናው ይለያይ እንጂ እሱም የልጅነት ምኞቱን በፈተና ማሳካቱን ነው የሚናገረው። « እድለኛ ነኝ ብዩ አስባለሁ። ሀገርን ወክሎ ለመጫወት ብዙ ፈተናዎች አሉት» ሱራፌል ባህር ዳር ላይ ከአይቮሪኮስት ጋር በተደረገው ግጥሚያ ጎል አስገብቷል።  ማላዊም ላይ እንዲሁ ጎል አስገብቷል።

Äthiopien Addis Abeba | Fans feiern Fußball Nationalmannschaft
አዲስ አበባ ውስጥ ለብሔራዊ ቡድኑ ድጋፋቸውን የሚገልፁ ኢትዮጵያውያንምስል Minasse W. Hailu/AA/picture alliance

ኢትዮጵያ ለአፍሪቃ ዋንጫ ለማለፍ ባደረጋችው ግጥሚያ በአይቮሪኮስት 3 ለ 1 ብትሸነፍም በዕለቱ የተጫወቱት ኒጀር እና ማዳጋስካር 0 ለ 0 መውጣታቸው ቀድሞውንም 9 ነጥብ ላሰባሰበችው ኢትዮጵያ ወደ አፍሪቃ ዋንጫ እንድታልፍ በር ከፍቶላታል። እግር ኳስ የቡድን ጨዋታ ቢሆንም አንድ ቡድን ሲያሸንፍ ወይም ሲሸነፍ ቀልብ ውስጥ የሚገቡት ግብ አስቆጣሪዎቹ ወይም ግብ ጠባቂዎቹ ናቸው። ግብ ጠባቂው ተክለማሪያም የብዙ ሰው ትኩረት ስለሚፈጥረው ተፅዕኖ በሚገባ ያውቃል። « ብዙም ባይሆን የተለየ ትኩረት ይፈልጋል። እና ግብ ጠባቂ መሆን ጫና አለው ።» ግብ ጠባቂነት ምኞቱ አልነበረም። ይልቁንስ ለእግር ኳስ ጨዋታ ዝዋይ ላይ ለአንድ ፕሮጀክት ሲመዘገብ፣ የተጫዋች ቦታ እንደሞላ ተነግሮት ያገኘው የግብ ጠባቂነት ቦታን ብቻ በመሆኑ ነው። እግር ኳስ ሕይወቴ ነው የሚለው ተክለማርያም ከዝናው እና ሀገሩን ከማገልገል ባሻገር «ቤተሰቤን የማስተዳድርበት የገቢ ምንጬ ነውም» ይላል።  በምዕራቡ ዓለም ባሉ ሀገሮች  እግር ኳስ የሥራ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፤ በተለይ አንደ አንድ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ብዙ ገንዘብ የሚካበትበትም ነው። እንደ ሱራፌል ከሆነ ኢትዮጵያውያኑ ተጫዋቾች ከግል ጥቅማቸው የበለጠ ትልቅ ስፍራ የሚሰጡት የሀገራቸውን ስም በበጎ ማስጠራቱ ላይ ነው።« አላማችን ለአፍሪቃ ዋንጫ ማለፍ ላይ ነው፤ ሀገራችን ሰላም እንድትሆን ፣ ጥሩ ውጤት አምጥተን ህዝባችን እንዲደሰት ነው። ከዚህ በላይ ሽልማት የለም፣ ከገንዘብ በላይ ነው። »

 ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ