1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

ሁኔታዎች ያልገደቧት «ሰቃይዋ» ተማሪ እና ህልሟ

ዓርብ፣ ሐምሌ 14 2015

የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን የታላቅ ወንድሟን እና እህቷን ፈለግ በመከተል የነርስ ሙያ ለመከታተል ነበር ነቀምቴ ወደ ሚገኘው የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ቅርንጫፍ ያመራችው ። በውጣ ውረድ ውስጥ ያሳለፈቻቸው የትምህርት ዓመታት ኦብሲኔትን አልከዷትም።

https://p.dw.com/p/4U9Du
Äthiopien |  Obsinet Garoma
ምስል Privat

የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን 99 ከ 100 ያመጣችው ኦብሲኔት ጋሮማ

ለመጀመሪያ ጊዜ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሰጠው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ውጤት ከሰሞኑ ይፋ ተደርጓል። ውጤቱ በመንግስት እና የግል ዩኒቨርሲቲዎች ለዓመታት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ሊመረቁ ከጫፍ ከደረሱ ተማሪዎች መካከል ብቁ ሆነው የተገኙት 40 ከመቶ ገደማ ያህል ተማሪዎች ናቸው ። ከ50 ከመቶ በላይ  ውጤት አምጥተው ማለፋቸውን ካረጋገጡ ተማሪዎች መካከል ደግሞ የነቀምቴዋ ኦብስኔት ጋሮማ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ቀዳሚ መሆኗ ተሰምቷል። ጤና ይስጥልን አድማጮች የዕለቱ የወጣቴች ዓለም ዝግጅታችንም ውጤታማዋ ተማሪ ጅምር የስኬት መንገድ ይቃኛል  ።
ትውልድ እና ዕድገቷ ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ከተማ 02 ቀበሌ ውስጥ ነው ። የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም እዚያው በትውልድ መንደሯ ነው የተከታተለችው ። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ደግሞ የታላቅ ወንድሟን እና እህቷን ፈለግ በመከተል የነርስ ሙያ ለመከታተል ነቀምቴ ወደ ሚገነኘው የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ  ቅርንጫፍ አመራች። በውጣ ውረድ ውስጥ ያሳለፈቻቸው የትምህርት ዓመታት ኦብሲኔትን አልከዷትም። ይልቁንም   ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ባደረገችው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ወይም exit exam ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ተማሪዎች 99 ከ 100 በማምጣት አንደኛ እንድትወጣ አስቻላት እንጂ ። ውጤቷን በተመለከተ ኦብሲኔት ስትናገር 
« መጀመሪያ ውጤቴን እንደሰማሁ በጣም ነው ደስ ያለኝ ፤ የምናገረውን ነው ያጣሁት ፤ ፈጣሪዬን አመሰገንኩ ፤ በጣም ነው በራሴ የኮራሁት ፤ በጣም ነው በራሴ የተደሰትኩት »
እውነት ጥረት ሲሰምር ፤ ድካምም ውጤት ሲያፈራ በራስ ስራ እንደመደሰት በራስ ስራ እንደመኩራት ምን አለና? 
ኦብሲኔት ከወላጅ ፍቅር እና እንክብካቤ ካደገችበት ሰፈር ስትወጣ አንድ ሕልም ነበራት «ከመጀመሪያው የግል ዩኒቨርሲቲ ወደ ሆነው ሪፍት ባሊ ዩኒቨርሲቲ የገባሁት ታላቅ እህቴ እዚሁ ዩኒቨርሲቲ የነርስ ትምህርቷን እየተከታተለች ስለነበር ወላጆቼ እዚያው ሂጄ ከእህቴ ጋር አንድ ላይ እንድማር አድርገውን ነው። እኔም ደግሞ ይህንኑ ትምህርት ለማጥናት የልጅነት ህልሜ ስለነበረ ነው። 
ገና ከመጀመሪያው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤቴ በራሱ ከፍተኛ ነበር። ይህንን ትምህርት ለመከታተል በራሱ ፈተና ተፈትኜ እና ጥሩ ውጤት አምጥቼ ነው የገባሁት ። በወቅቱ በርካታ ተማሪዎች ናቸው ከአጠገቤ የቀሩት ። »
ልጆች በትምህርታቸው በርትተው የተሻለ ውጤት አምጥተው ከራሳቸው ተርፈው ለሀገር ገጸ በረከት ሊሆኑ እንደሚችሉ ኦብሲኔትን ጨምሮ በርካቶችን አይተናል አልያም ታሪካቸውን ሰምተናል። ለኦብሲኔት የትምህርት መንገድ መቃናት ወላጆቿ የነበራቸው ሚና ትልቅ እንደበር ነው አጽንዖት ሰጥታ  የምትናገረው። 
«ለወላጆቼ አራተኛ ልጅ ነኝ ። ወላጆቼ ከእኔ በፊት ሁለት ወንድ ልጆች እና አንዲት ሴት ልጅ አላቸው። ወላጆቼ ለትምህርት እጅግ በጣም ትልቅ ቦታ ነው የሚሰጡት ። ከፈጣሪ ቀጥሎ በትምህት ነው የሚያምኑት ። በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ፤ ከምንም ሃብት እና ንብረት በላይ ትምህርት ያስቀድማሉ፤ ግባቸውም ትምህርት ነው። የተማረ ወድቆ አይወድቅም ብለው ነው የሚነግሩን ። ለዝህም ነው ግባችንም ሙሉ ትኩረታችንም ትምህርት እንዲሆን ነው እየመከሩ ያሳደጉን።»
ዶ/ር ጂራታ ጋሮማ የኦብሲኔት ታላቅ ወንድም ነው። ወጣት ነው። ለኦብሲኔት እና ታላቅ እህቷ የህክምና ትምህርት መርጠው እንዲማሩ አርአያ የሆናቸው ወንድም ነው።  የቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ ነው። ኦብሲኔት ያስመዘገበችው ውጤት እንዳስደሰተው ይናገራል። 
«ውጤቱን እንደሰማሁ ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ ኤግዚት ኤግዛም ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ ይህን ውጤት ታመጣለች ብለን አላሰብንም፤ ነገር ግን እን,ጠበቅነው ሳይሆን እርሷ ከፍተኛ ውጤት በማምጣቷ ከፍተኛ ደስታ ነው የተሰማኝ  »
ኦብስኔት ምስክርነቷን እንደሰጠችው ሁሉ ለቤተሰቡ በሙሉ የትምህርት መንገድ መቃናት በተለይ በመምህርነት ሞያ የተሰማሩት አባታቸው አቶ ጋሮማ ቴሶ ፍላጎት እና ጥረት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ። ወጣቱ ሀኪም ጂራታ ጋሮማ ምስክርነትም ይኸው ነው። 
« ቤተሰባችን ለትምህርት ትልቅ ቦታ ነው ያለው ።በተለይ አባታችን መምህር ስለነበረ ለትምህርት ያለው ቦታ እና ትኩረት በጣም ከፍተኛ ነው። ሁላችንም ተምረን ትልቅ ደረጃ እንድንደርስ ነው የእርሱ ፍላጎት ማለት ነው»
ምንም እንኳ  ልጆች የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው የወላጆች ያላሰለሰ ጥረት ወሳኝ ቢሆንም ፤ ጥረት በፍላጎት ታግዞ ፍሬ እንዲያፈራ ደግሞ የልጆች ተነሳሽነታቸው እና እርስ በእርስ የመደጋገፍ ኃላፊነታቸውን መወጣት የግድ ይላል። የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች በከፍተኛ የጸጥታ ችግር ውስጥ በሆነበት እና መረጋጋት በራቀበት በዚህ ጊዜ በእርግጥ ይህ ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ድጋፋቸው እንዳልራቃት ነው ጂራታ የሚናገረው።
«ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ አለመረጋጋት እንደነበር፤ ባለፉት ጥቂት አመታት ብዙ ችግር ነበር እና በዚያ ላይ ትምህርት ላይ ወላጆች ላይ ተጽዕኖ ነበረው ማለት ነው። በትኩረት እንዳይማሩ ያደርጋል ። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሆና በንጽጽር ትምህርቷ ላይ ብቻ አተኩራ እንድታነብ ነበር የእኛ ጥረት ።» 
የጊዜው እና የሁኔታዎች አስቸጋሪነት በእርግጥ አያጠያይቅም ። ኦብሲኔትም ይህንኑ ትጋራለች። መሰረታዊው ነገር ግን ጊዜውን በትዕግስትእና ሸሸግ ብላ አላማዋን ለማሳካት በእጇ የነበሩትን የማጥኛ አማራጮች ከመጠቀም ግን አላገዳትም።
«ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ እጅግ በጣም አስቸጋሪ እና ውስብስብ ነው። ያለፍንበትም ሆነ ያለንበት ሁኔታም ልዩነት የለውም ። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ሆነንም ፤ ምንም እንኳ የደህንነት ስጋት ውስጥ በነበርንበት ጊዜ ውስጥ ትምህርት ቤት ሲዘጋ በቆየበት ጊዜም እጃችን ላይ ያሉ መጽሐፍት እና ሶፍት ኮፒዎችን ቤታችን ሆነን እያነበብን ነው በትዕግስት ያለፍነው። »
ኦብሲኔት ጋሮማ ላስመዘገበችው ከፍተኛ ውጤት ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁ ቸል ብሎ አልተመለከተም። ከራሷ ከተማሪዋ አንደበት እንደሰማነው እና እንደተረዳነው ። ዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ከማመቻቸት በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲው በመረጠችው ካምፓስ የስራ ዕድል አዘጋጅቶላታል። ምንም እንኳ አፈጻጸሙ በንግግር ሂደት ላይ ቢሆንም ። 
በዩኒቨርሲቲው የነቀምቴ ካምፓስ የጤና እና ቴክኖሎጂ ፋካሊቲ ዲን የሆኑት አቶ አማኑኤል ተስፋዬ እንደሚሉት ኦብሲኔት ጋሮማ ባልተመቻቸ የትምህርት ሁኔታ ውስጥ ሆና ይህን ውጤት ማምጣቷ የሚያመሰግን ነው። 
« ብዙ የትምህርት መሳሪያ እና አካባቢ ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ናቸው እየተጠበቁ የነበሩት። እና ግን በግል እንደሚታወቀው በቂ የሚባል ቁሳቁስ እና አስፈላጊ ናቸው ተብለው የሚጠየቁ ቁሳቁሶች ሳይኖሩ ነው ውጤቱ የተመዘገበው፤ እንደዚያም ሆኖ ግን ልጅቷ ጥሩ ውጤት አምጥታለች። »
ለውጤቷ ማማር ደግሞ ተማሪዋ በግሏ ታደርግ የነበረው ጥረት ጎልቶ እንደሚጠቀስ ነው አቶ አማኑኤል የነገሩን ። 
«ያው ልጅቷ በጣም የሚገርመው ከቤተምሐፍት አትጠፋም። በስልኳ ላይ የምትጠቀማቸው የትምህርት ሰነዶች አንዳንድ ፋይሎች ጥያቄዎች ፤ ከ2008 ጀምሮ የነበሩ የፈተና ጥያቄዎች በማንበብ ራሷን እያዘጋጀች ነበር።»
ኦብሲኔት ከፍተኛ ውጤት አመጣሁ ብላ እንዳማትዘናጋ ነው ለዝግጅት ክፍላችን የነገረችው ። ያገኘቻቸውን ዕድሎች እየተጠቀመች ነገር ግን በዚሁ የጤና መስክ ከፍተና ደረጃ ለመድረስ ራዕይ መሰናቋን ጭምር ገልጻልናለች
« አሁንም ቢሆን ይኽንኑ አጠናክሬ መቀጠል ነው የምፈልገው ፤ ይህንን ሳልለቅ በጤና ትምህርት ቀጥዬ መማር ነው የምፈልገው፤ ራዕዬን ለማሳካት ማጥናት የምፈልገው የትምህርት አይነት አለኝ  »
እውነት ነው፤ አላማዬ ብለው ከያዙት ምንም እንኳ ሁኔታዎች ተጽዕኖ ቢያሳድሩም ከቶ ማስቆም እንደማይችሉ ከብዙ ማሳያዎች የኦብሲኔት ጋሮማ ቅንጭብ የትምህርት ህይወቷ ይመሰክራል። ዋናው ጤና እንጂ ማን ያውቃል ነገ ከአንጋፋዎቹ  ሐኪሞች ተርታም እናያት ይሆናል። 
በነገራችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ በተደረገው በዚሁ የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተናን ከወሰዱ 150 ሺህ ተማሪዎች መካከል የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት 40.65 በመቶ ብቻ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴርን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል። የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካስፈተኗቸው ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡት ደግሞ 17.23 ብቻ ነበር ። 
ታምራት ዲንሳ 
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር 
 

Äthiopien | Jirata Garoma
ምስል Privat
Äthiopien |  Obsinet Garoma
ምስል Privat