1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጃራ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 22 2015

ከአላማጣ ከተማ ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ጃራ የመጠለያ ጣቢያ ከአንድ ዓመት በላይ ይኖሩ የነበሩ የአላማጣ ከተማ ተፈናቃዮች በመንግስት ድጋፍ ትናንት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የአካባቢው አስተዳደርና ተፈናቃዮች ተናገሩ፣ በመጠለያ ጣቢያው ከአላማጣ፣ ባላ፣ ኮረምና ኦፍላ የተፈናቀሉ ከ 30 ሺህ በላይ ሰዎች ይኖሩበት ነበር ተብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/4IvCy
Äthiopien Binnenvertriebene aus Alamata kehren zurück
ምስል Sintayehu Seid/Alamata Youth League

ከአላማጣ ከተማ ተፈናቅለው በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ጃራ የመጠለያ ጣቢያ ከአንድ ዓመት በላይ ይኖሩ የነበሩ የአላማጣ ከተማ ተፈናቃዮች በመንግስት ድጋፍ ትናንት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የአካባቢው አስተዳደርና ተፈናቃዮች ተናገሩ፣ በመጠለያ ጣቢያው ከአላማጣ፣ ባላ፣ ኮረምና ኦፍላ የተፈናቀሉ ከ30ሺህ በላይ ሰዎች ይኖሩበት ነበር ተብሏል፡፡ እነኚህ ተፈናቃዮች በአብዛኛው የአማራ ማንነት ያላቸው እንደሆኑ የአላማጣ ከተማ አስተዳደር የወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ሰኢድ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

Äthiopien Binnenvertriebene aus Alamata kehren zurück
የጃራ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አላማጣ እየተመለሱ ነውምስል Sintayehu Seid/Alamata Youth League

ለአንድ አመት ከ4 ወራት በጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ከነበሩት ተፈናቃዮች መካከል የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ትናንት መመለሳቸውንም አቶ ስንታየሁ አመልክተዋል፡፡

“የአላማጣ ከተማ ነዋሪ ከሞላ ጎደል (ከ98-99 ከመቶ) ዛሬ ተጠቃልሎ ይገባል፣ ከአንድ ላይ ነው… ባሶቹ፣ በግል የሚሄዱት ተሸከርካሪዎች አብረው ያው እቃ የያዙት የእኛም አመራሮች ከአላማጣ መጥተው ቆቦ ድረስ እኛን ለመቀበል መትተዋል፣ የአላማጣ ህዝብም ከጠዋት ጀምሮ ከተማው ላይ ወጥቶ እየጠበቀን እንደሆነ ነው ለኝ መረጃ”

የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ዘነብ ወርቅ ጣውዬ በበኩላቸው

ተፈናቃዮቹ በተለያዩ ተሸከርካሪዎች በደስታ በመንግስት አካላት ታጅበው እየተመለሱ እንደሆነ አስረድተዋል

“የጭነት መኪና አለ ዱቄት የጫነ፣ ሻንጣ፣ ፍራሽና ሌሎች እቃዎች የያዙ  ክብደት የሌላቸውን በየባሱ፣ ሰሜን ወሎ ምግብ ዋስትኛዎች ባሉበት ነው ታጅበን እየሄድን ያለነው፣ በጣም አሪፍ ነው፣ ደስ ይላል፣ ሁላችንም መትተናል 60 ያህል ብቻ ናቸው የአላማጣ ተፈናቃዮች የቀሩ”

Alamata Flüchtlingsunterkünfte Jara in Region Amhara
ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ምስል Alamata City Youth League

ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ እንዳይቸገሩ አንዳንድ ተቋማት ድጋፍ ማድረጋቸውንም መምሪያ ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

“ እርዳታ ተሰጥቶናል፣ ቃለ ህይወት የተባለው ድርጅት ዱቄት ዘይትና ባቄላ ሰጥቷል፣ መካነየሱስ የተባለው ተቋም ደግሞ ዱቄት ለመጫቶች ፋፋና ዘይትና ቦሎቄ ፣ ሲአርኤ ደግሞ ከ14-18 ዓመት ለሆናቸው ልጃገረዶች የንፅህና መጠበቂያና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከአላማጣ ከወጣን አንድ ዓመት ከ4 ወራችን ነው ”

በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ አወል ሁሴን የአላማጣ ከተማ  ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ጠቁመው የሌሎች ተፈናቃዮች የጉዞ ፕሮግራምም መዘጋጀቱን ለዶይቼ ቬለ ገልጠዋል፡፡

“በይፋ አንቀሳቅሰናል፣ እንግዴህ ህዝቡም በዚሁ ልክ እየወታ ስለሆነ መማገዙን ጀምረነዋል፣ ትልልቁ አውቶቡስ ወትቷል እስከመጨረሻው እንቀትላለን፡፡ የአላማጣ ከተማ በሙሉ ወጥቷል ማለት ይቻላል፣ የተንጠባጠቡ ብቻ ናቸው የሚቀሩት፡፡ የተለያዩ ድርጅቶች ደግፈውልናል፣ በመንግስትም የደገፍነው አለ፣ ለአንድ ወር የሚበቃ ቀለብ ይዘው ሄደዋል፣ አይቸገሩም ብዬ አስባለሁ፡፡”

አንድ በጉዞ ላይ ሆነው አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ተመላሽ ህዝቡ በየመንገዱ ሆኖ መልካም አቀባበል አድርጎልናል፣ ደስ ብሎናል ብለዋል፡፡

Äthiopien Alamata City Gondar
ተፈናቅለዉ የነበሩ ነዋሪዎች ወደ አላማጣ ከተማ እተመለሱ ነውምስል Alemnew Mekonnen/DW

“በጣም ደስ የሚል ድባብ ነው ያለው፣ ህብረተሰቡ ድጋሜ እንደተወለደ ዓይነት ስሜት ነው የሚሰማው፣ ወጣቱም አዛውንቶችም፣ በአንድ “የተስፋይቱን መሬት” አሁን እያየናት ነው እየቀረብን ነው አሁን ልንገባ ፣ ደስ የሚል ነው ወጣቱ እየጨፈረ ነው፣ እናቶች በእልልታ፣ አካባቢው በፀጋ እተቀበለን ነው መንገደኛው፣ በእግር የሚያልፈው ሁሉ በሰላምታ፣ እንኳን ወደ አገራችሁ ገባችሁ እለ ደስታውን እየገለፀልን ነው ያለው አሁን፡፡”

በሰሜኑ ጦርነት በአማራ ክልል ብቻ 2 ሚሊዮን 300 ሺህ ህዝብ የተፈናቀለ ሲሆን 1 ሚሊዮን አንድ መቶ 15 ሺህ በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኝ ነው፣ ቀሪው በየዘመድ አዝማዱ ተጠልሎ ይኖራል፣ በጦርነቱ ሰበብ 11 ሚሊዮን ህዝብ  ለምግብ እጥረት የተዳረገ እንደሆነም በቅርቡ ይፋ የሆነ ጥናት አመልክቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተፈናቃዮቹ የምግብ እጥረትና የደህንነት ስጋት አለብን በሚል ቅሬታቸውን ተቀብለን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ

ሽዋዬ ለገሰ