1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚያዚያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Lidet Abebeቅዳሜ፣ ሚያዝያ 19 2016

የኦፌኮ አመራሮች እስራት፤ የፓርቲው መግለጫ ሩዋንዳ፤ ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውንጀላ ምላሽ ሰጠች ቤኒን፤ ፖሊስ ሰልፈኞች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኮሰ ሃማስ አዲሱን የእስራኤል የእርቅ ሃሳብ እንደሚያጤን አስታወቀ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጥሪ አትሌት መዲና ኢሳ በ 5ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ሰበረች

https://p.dw.com/p/4fG9s

የኦፌኮ አመራሮች እስራት፤ የፓርቲው መግለጫ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ገዢው መንግሥት አመራሮቼ እና አባላቶቼ ላይ የሚያደርሰው እስራት እና ከህግ አግባብ ውጪ የሚፈፀም ግድያ አማሮኛል ሲል የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመለከተ። ፓርቲው ይህንኑን አስመልክቶ ትናንት ዓርብ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ እየደረሰብኝ ነው ያለው የአመራሮች እና አባላት እስራት እንዲሁም ከህግ አግባብ ውጪ የሚፈፀም ግድያ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አቋሙንም እንደሚያናውጥ አሳውቋል። የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ስለመግለጫው ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ከሰሞኑ ስምንት የኦፌኮ አመራሮች በኦሮሚያ ክልል በኃይል መሰወራቸውን ለዓብነት ገልፀዋል። ከህግ ውጪ ስወራና ግድያን ጨምሮ የተለያዩ አላስፈላጊ እርምጃዎች በፓርቲው አመራሮች እና አባላት ላይ መፈፀሙ ፓርቲውን በእጅጉ እንዳሳሰበውም ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለDW  አብራርተዋል። ስለሆነውም ሁሉም የሀገሪቱ የፖለቲካ እስረኞች በአፋጣኝ እንዲፈቱ እንዲሁም ገዢው ፓርቲ ህገ መንግስቱን እንዲያከብር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንዲያሳርፍ ኦፌኮ ጠይቋል። ኦፌኮ ስላቀረበው ክስ እስካሁን የተሰማ የመንግስት ምላሸ እንደሌለ ሥዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ ዘግቧል። ዝርዝሩ ከዓለም ዜና በኋላ ይቀርባል።

 

ሩዋንዳ፤ ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውንጀላ ምላሽ ሰጠች 

የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መንግሥት በአፕል ኩባንያ ላይ የሰነዘረው ክስ "መሠረተ ቢስ ውንጀላ" ነው ሲል የሩዋንዳ መንግሥት አጣጣለ። የሩዋንዳ መንግሥት ይህን ያለው ግዙፉ አፕል ኩባንያ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል  ወደ ጎረቤት ሀገር ሩዋንዳ በህገ-ወጥ መንገድ የሚገቡ ማዕድናትን በመግዛት ወደ ሌሎች አለምአቀፍ አከፋፋዮች ያሰራጫል በማለት ከወነጀለች ከአንድ ቀን በኋላ ነው። ፓሪስ የሚገኙ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠበቆች ሀሙስ ዕለት አፕል በዚህ ድርጊቱ ከቀጠለ ህጋዊ እርምጃ ሊጠብቀው እንደሚችል የላኩት ማስጠንቀቂያ ግልባጭ እንደደረሰው አዣንስ ፍራንስ አክሎ ገልጿል። የሩዋንዳ መንግሥት ቃል አቀባይ  ዮላንዴ ማኮሎ “መሰረተ ቢስ ክሶችን እና ግምቶችን በማሰራጨት በአለም ላይ ካሉት ትልልቅ ኩባንያዎች አንዱ የሆነው አፕልን ስም በማጥፋት የመገናኛ ብዙኃን ፍላጎትን ለመሳብ የተደረገ ሙከራ ነው »ሲሉ ውንጀላውን አጣጥለዋል። 
ከዚህም ሌላ ቃል አቀባይዋ ይህ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሩዋንዳ ላይ በተደጋጋሚ ከሰነዘረችው ኃሰተኛ ውንጀላዎች የቅርብ ጊዜው ነው ብለዋል። ለዘመናዊ ስልኮች እና ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ግብዓት በሚሆኑ ማዕድኖች የታደለችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሰዉን M23 አማፂ ቡድን ሩዋንዳ ትደግፋለች በሚል በተደጋጋሚ ሀገሪቱን መወንጀሏ ይታወሳል። የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ውንጀላውን አስተባብለው በበኩላቸው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኪጋሊ ያለ የሁቱ ሚሊሽያን ትደግፋለች ሲሉ ይወቅሳሉ።
 

ቤኒን፤ ፖሊስ ሰልፈኞች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኮሰ

የቤኒን ፖሊስ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎችን በአስለቃሽ ጭስ  መበተኑን በስፍራው የነበረ የዣንስ ፍራንስ ፕረስ ወኪል ገለፀ። መጠነኛ ቁጥር ነበራቸው የተባሉት ሰልፈኞች  ያለውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት በመቃወም የኢኮኖሚ ማዕከል በሆነችው ኮቶኑ ከተማ ነበር ዛሬ አደባባይ የወጡት። 
በፖሊሶች ተከቦ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገኙት ሰልፈኞች የሀገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር ይዘምሩ እንደነበርም ተዘግቧል። በሀገሪቱ ካሉ የሰራተኛ ማህበራት ትልቁ የሚባለው እና የዛሬው ሰልፍ አስተባባሪ CSA ቤኒን በ X የማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው ከማህበሩ መሪ  በተጨማሪ ሌሎች 12 በሰልፉ ላይ የተገኙ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል። ፖሊስ ስለ ድርጊቱ መግለጫ አልሰጠም።
 

ሃማስ አዲሱን የእስራኤል የእርቅ ሃሳብ እንደሚያጤን አስታወቀ

የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ እና በርካታ አለም አቀፍ ባለስልጣናት በሳምንቱ መጀመሪያ ሳዑዲ አረቢያ ሪያድ ተገኝተው በጋዛ ሰላም የሚሰፍንበት ስምምት ላይ እንደሚወያዩ ተገለፀ።  የዓለም የኤኮኖሚ ጉባኤ  ፕሬዚዳንት ዛሬ እንደገለፁት ስብሰባው የሚካሄደው ሰኞ በሚጀምረው የዓለም የኤኮኖሚ ጉባኤ ጎን ለጎን ነው። ፕሬዚዳንት ቦርጌ ብሬንደ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት "ቁልፍ ሚና ተጫዋቾች በዚያው በሪያድ ስለሚገኙ የሚካሄዱት ውይይቶች ወደ እርቅ ሂደት ሊያመሩ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል። በጉባኤው ላይ የዩናይትድ ስቴትስ እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የባህሬን ባለስልጣናት እንደሚገኙ ሮይተርስ ዘግቧል።  
የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚህ ሹክሪ የግብፅ ተደራዳሪዎች አርብ ዕለት እስራኤል ውስጥ የጋዛን ጦርነት አቁሞ የቀሩትን የእስራኤል ታጋቾች ለማስፈታት ስላደረጉት ጥረት ከምን እንደደረሰ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። 
የሀማስ ቡድን በበኩሉ ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ ከእስራኤል የቀረበውን አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት አጤኖ ምላሽ እንደሚሰጥ ዛሬ አስታውቋል።
 

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጥሪ

ሩሲያ ሌሊቱን የዩክሬን ኃይል ማመንጫ ላይ የሰነዘረችውን የአየር ጥቃት ተከትሎ  የአየር መከላከያ እና ፈጣን የጦር መሣሪያዎች እንዲቀርብላቸው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ አዲስ ጥሪ አስተላለፉ። ዘሌንስኪ እንዳሉት ዩክሬን በቂ መጠን ያለው የሚሳኤል ማክሸፊያ እና ሌሎች የጦር መሣሪያዎች ከተሞቿን ለመጠበቅ እና ለማሸነፍ ያስፈልጓታል። "ሽብር ሁል ጊዜ መሸነፍ አለበት።  እኛን የሚረዳን ሁሉ ሀቀኛ የሩሲያ ሽብርን ተቃዋሚ ነው" ብለዋል ዘሌንስኪ። 
እንደ ዩክሬን ገለፃ ሩሲያ ዛሬ በሦስት ክልሎች በሚገኙ የኃይል ማመንጫዎች ላይ ብርቱ ጥቃት ሰንዝራ ሁለት የኃይል ሰራተኞች ሲገደሉ አራት የኃይል ማመንጫዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። 
ዩክሬን እንዲሁ ከአንድ ወር ገደማ በፊት በሩሲያ ሚሳኤል  እና ሰው አልባ አይሮፕላኖች በነዳጅ እና ኃይል ማመንጫ ዘርፏ ላይ ብርቱ ጉዳት መድረሱን አስታውቃ ነበር።  ሩስያ እስከ ባለፈው ህዳር ወር ድረስ ከ 60 ጊዜ በላይ በኃይል መሠረተ ልማቷ ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ዩክሬን አስታውቃ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩክሬን ዛሬ በደቡብ ሩሲያ በሚገኙ ሁለት የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ፋብሪካዎች ላይ የተሳካ ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች። ከዚህም ሌላ ዩክሬን ሌሊቱን በከባድ ሰው አልባ አውሮፕላን አንድ ወታደራዊ አየር ማረፊያ ላይ ጥቃት መፈፀሟን አስታውቃለች።  የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን  በአንዱ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ፋብሪካ ላይ ቃጠሎ መነሳቱን እና ስራ በከፊል መቋረጡን ዘግበዋል። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በዩክሬን ሰው አልባ አይሮፕላኖች ጥቃት አምስት ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቋል።
 

አትሌት መዲና ኢሳ በ 5ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ሰበረች

አትሌት መዲና ኢሳ በ5ሺህ ሜትር ከ20 ዓመት በታች የሩጫ ውድድር የዓለም ክብረ ወሰን ሰበረች። የ19 ዓመቷ መዲና ዛሬ  በሄርዞግንአውራህ ጀርመን የተካሄደውን ውድድር የጨረሰችው 14 ደቂቃ ከ 38 ሰከንድ በመሮጥ እንደሆነ አዲዳስ በ X የማህበራዊ ትስስር ገፁ አስታውቋል።  የአዲዳስ ኩባንያ አዲዜሮ ሮድ ቱ ሪኮርድስ ባዘጋጀው በዚሁ የሴቶች ውድድር አትሌት መልክናት ውዱ 2ኛ ፣ ፎቲየን ተስፋይ 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቀዋል፡፡ 4ኛ ከወጣችው ኬንያዊት በቀር እስከ 8ኛ የወጡት ኢትዮጵያዊያን ነበሩ።
በወንዶች ኢትዮጵያዊያኑ ዮሚፍ ቀጀልቻ 13 ደቂቃ  ከ 00 ሰከንድ በመግባት አሸንፏል።  የሀገሩ ልጅ ይሁኔ አዲሱ 2ኛ  ወጥቷል። ለባህሬን የሚሮጠው ብርኃኑ በለው ሶስተኛ ሆኖ አጠናቋል።
 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።