1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"እኛ ለትግራይ ዓለም ነን" ለትግራይ የእርዳታ ማሰባሰቢያ መርሐግብር

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 2016

በትግራይ ለ2 ዓመት በተካሄደው ጦርነት ለደረሰው ሰብዓዊ ችግር ለመድረስ "እኛ ለትግራይ ዓለም ነን" የተሰኘ ዓለም አቀፍ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተጀመረ።አስተባባሪው ኘሮፌሰር ሙሉጌታ ገብረእግዚአብሄር ለዶይቸ ቨለ እንደገለጹት፣በትግራይ ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በኃላ የደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ ፣አስቸኳይ እርምጃ ያስፈልገዋል።

https://p.dw.com/p/4f8tV
 “We are the World for Tigray” in USA member of TPLF 2024
ምስል Mulugeta Gebregziabher

"እኛ ለትግራይ ዓለም ነን" ለትግራይ የእርዳታ ማሰባሰቢያ መርሐግብር

በትግራይ ለሁለት ዓመት በተካሄደው ጦርነት ለደረሰው ሰብዓዊ  ችግር "እኛ ለትግራይ ዓለም ነን" የተሰኘ  ዓለም አቀፍ  የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ተጀመረ። የመርሐግብሩ አስተባባሪ ኘሮፌሰር ሙሉጌታ ገብረእግዚአብሄር ለዶይቸ ቨለ እንደገለጹት፣በትግራይ ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በኃላ ያለው አስከፊ የሰብዓዊ ሁኔታ፣አስቸኳይ እርምጃ ያስፈልገዋል። 
አስተባባሪው ፕሮፌሰር ሙሉጌታ፣በደቡብ ካሮላይና ግዛት በሚገኘው ሜዲካል ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ሲሆኑ፣በቅርቡ ለሦስት ሳምንታት ያህል በትግራይ ጉብኝት አድርገው ተመልሰዋል። 

በትራግይ የሚስተዋለው የሐዘን ድባብ 

በትግራይ ከጦርነቱ በኋላየተመለከቱትን አስከፊ ሁኔታም እንደሚከተለው ገልጸውታል። "በመገናኛ ብዙሃን እየተዘገበ ያለውን ርሃብ በዐይኔ ዐይቼዋለኹ።የውኃ፣የምግብ እጥረት እንደዚሁም ተፈናቃዮችን ከተፈናቀሉበት ቦታ ሳይወጡ ችግር ላይ እንዳሉ አይቼዋለሁ። ሌላው ብዙ ሰው ስለሞተ የሐዘን ድባብ በጣም አጥልቶበታል።ከተሞችም ገጠሮችም በየኼድኹበት ሦስት ሳምንት ብዙውን በየሄድኹበት ለቅሶ ቤት አለ።የታመሙትን ማጽናናት አለና ይኼ ሁሉ ችግር አለ።በዚሁ ላይ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት አሉ።ሌሎች የማኀበረሰብ መገልገያ  ተቋማት ወደመዋል።


የትግራይ እናት ከልጅ ልጆቿ ጋር
የትግራይ እናት ከልጅ ልጆቿ ጋር ምስል Ed Ram/Getty Images

የጤና ተቋማት ውድመት

ፕሮፌሰር ሙሉጌታ እንዳሉት፣በትግራይ ከጦርቱ በፊት አንድ ሺህ ሰባት የጤና ተቋማት ነበሩ። ከጦርነቱ በኃላ ግን፣ ከአስከፊው ረሃብና በሽታ በተጨማሪ፣ከሆስፒታሎች ሦስት ነጥብ ስድስት፣ከህክምና መሣሪያዎች ደግሞ አንድ በመቶ ብቻ ነው የተረፉት፣የተቀሩት በሙሉና በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
"እኛ ለትግራይ ዓለም ነን"የተሰኘው የሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐግብር፣በኢትዮጵያ ተከስቶ ለነበረው ከባድ ረሃብ ከመላው ዓለም ዕርዳታ ለማሰባሰብ የዛሬ 39 ዓመት የተሰራውን"እኛ ዓለም ነን"ዜማ መነሻ ያደረገ ነው፤ይላሉ አስተባባሪው።

"እኛ ለትግራይ ዓለም ነን"

"ዓለም ኢና ንሕና በትግራኛ፣በግእዝ ውእቱ ዓለም ንሕነ እኛ ለትግራይ ዓለም ነን የ39ኛውን በዓል መርሐ ግብር አዘጋጅተን እያከበርን ነው። ፕሮግራሙ ኤፕሪል ሃያ ባለፈው ቅዳሜ ነው  የተጀመረው እስከሚቀጥለው እሁድ ይቀጥላል።ዓላማው ምንድነው ጦርነቱም ይሁን ረሃቡም ይሁን ድርቁም  ሁሉም ችግሮች በየዘመኑ እየመጡ ነው።በየአምስት ዓመቱም ሆነ በየዐስር ዓመቱ ብቻ ከእዛ አልተላቀቅንም።

በትግራይ እናቶችና ህጻናት የሚወስዱት ውሀ እስኪመጣ ሲጠባበቁ
በትግራይ እናቶችና ህጻናት የሚወስዱት ውሀ እስኪመጣ ሲጠባበቁ ምስል Haileselassie Million/DW

39 ዓመታት አለፉ ግን አሁንም እዛው ነው ያለነው።እና ማስታወስ ይገባል ነው።ዓለምም አውቆት ዘላቂ መፍትሔ እንድናፈላልግበት እሱ ነው ዋና ዓላማው።"
በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ስነሥርዓት በድረ ገጽ በኤክስ በማኀበራዊ ሚዲያ የተላለፈ ሲሆን፣በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ይከናወናል። አቀፍ ኮንፈረንስም ተዘጋጅቷል። በዝግጅቱ ላይ በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ማኀበረሰብ ተወላጆች፣ታዋቂ ግለሰቦችና በትግራይ ያሉ ዩኒቨርስቲዎችና ልዩ ልዩ ተቋማት አየተሳተፉበት መሆኑን፣ ከአስተባባሪው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል። በመርሐ ግብሩ ከሃምሳ ሺህ ዶላር በላይ ለማሰባሰብ መታቀዱን የገለጹት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ፣በትግራይ ያለውን ሰብዓዊ ችግር ለመፍታት፣ ጥረቱ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ታሪኩ ኃይሉ
ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ