1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ቲክ ቶክ በባለሥልጣናት ዘንድ ለምን ስጋት አሳደረ?

ረቡዕ፣ መጋቢት 13 2015

ቲክ ቶክ በአሁኑ ወቅት ተወዳጅ ከሆኑት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መካከል አንዱ ነው።ያም ሆኖ የተለያዩ ሀገራት ባለሥልጣናትን እያወዛገበ ነው።አሜሪካ፣ካናዳ እና ብሪታንያን ጨምሮ በርከት ያሉ ሀገራት ቲኪቶክ ከመንግስት ተንቀሳቃሽ የኤለክትሮኒክ መሳሪያዎች ላይ መታገዱን በቅርቡ አስታውቀዋል።ለመሆኑ ቲክ ቶክ በባለስልጣናት ዘንድ ለምን ስጋት አሳደረ?

https://p.dw.com/p/4P309
TikTok | Logo auf einem Mobiltelefon
ምስል The Canadian Press/AP/dpa/picture alliance

ቲክ ቶክ ቻይና እና አሜሪካን እያወዛገበ ነው


በአሁኑ ወቅት በጣም ተወዳጅ ከሆኑት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  መካከል ቲክ ቶክ አንዱ ነው።ያም ሆኖ መተግበሪያው የተለያዩ ሀገራት ባለሥልጣናትን እያወዛገበ ነው።መተግበሪያው በግል ተጠቃሚዎች ላይ እስካሁን እገዳ ባይጣልበትም ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፣ ካናዳ እና ብሪታንያን ጨምሮ ሌሎች በርከት ያሉ ሀገራት ቲኪቶክ  ከይፋዊ የመንግስት ተንቀሳቃሽ የኤለክትሮኒክ መሳሪያዎች ላይ መታገዱን በቅርቡ አስታውቀዋል።ለመሆኑ ቲክ ቶክ በባለስልጣናት ዘንድ ለምን ስጋት አሳደረ?የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ትኩረት ነው።
ቲክ ቶክ በዓለም ዙሪያ በጭር ጊዜ ውስጥ በጣም ተወዳጅ ከሆኑት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  ውስጥ አንዱ ነው።ከ3 ሰከንድ እስከ 10 ደቂቃ የሚቆዩ አጫጭር ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በማጋራት የሚታወቀው ቲክ ቶክ፤ ሃሳቡ የተጠነሰሰው በጎርጎሪያኑ  መስከረም 2016 ዓ/ም ባይትዳንስ በተባለው የቻይና  የቴክኖሎጂ ኩባንያ ነው።አጀማመሩም ተጠቃሚዎች አጫጭር ቪዲዮዎችን እንዲፈጥሩ እና እንዲያጋሩ የሚያስችል /A.me / ኤ.ሜ የተሰኘ መተግበሪያን በመስራት ነበር። ከሶስት ወር በኋላ ግን ይህ መተግበሪያ «ዶዪን» የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል። በ 2018 ዓ/ም ባይት ዳንስ  ሙዚክ ሊ/Musical.ly/  በሚል መጠሪያ ከሚታወቀው እና የሰዎችን የከንፈር እንቅስቃሴ ከሙዚቃ ጋር በማዋሃድ  አጫጭር ተንቀሳቃሽ  ምስሎችን እንዲፈጥሩ እና እንዲያጋሩ ከሚያደርገው መተግበሪያ ጋር ዶዩን በማዋሀድ  ቲክ ቶክ በሚል ስም ከቻይና ውጭ ማስፋፋት ጀመረ ። በዚህ ሁኔታ የተጀመረው ቲክቶክ፤ በአሁኑ ወቅት ከ150 በላይ ሀጎሮች ይጠቀሙበታል።  በ2022 መጀመሪያ ላይ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው መተግበሪያው በዓለም አቀፍ ደረጃ  ከ1 ቢሊዮን በላይ  ተጠቃሚዎች አሉት።ይህም ከሌሎቹ ሲነፃጸር ተወዳጅነትን ያተረፈው በአጭር ጊዜ ነው።የመረጃ ቴክኖሎጅ ባለሙያው እና የተራኪ መተግበሪያ መስራች የሆነው ናሆም ፀጋዬ  ሁለት ምክንያቶችን ያቀርባል። አንድም የሚጠቀመው ሰልተ ቀመር /አልጎሪዝም ሁለተኛ ደግሞ በዙ የይዘት ፈጣሪዎችን ማፍራቱ ነው።

Äthiopien | Nahom Tsegaye
ናሆም ፀጋዬ የመረጃ ቴክኖሎጅ ባለሙያ እና የተራኪ መተግበሪያ መስራችምስል privat

ከዚህ በተጨማሪ ቲክቶክ ለአጠቃቀም ቀላል እና  በተለያዩ መስኮቶች  ነገር ግን በአንድ ጊዜ  የተለያዩ  ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ማራኪ በሆነ መንገድ በአጭሩ የሚያሳይ በመሆኑ ተፈላጊነቱን አሳድጎታል።ከተራ የቤት ጨዋታ እስከ ሀገራዊ እና ጠጣር ፖለቲካዊ  ጉዳዮች በአጭሩ ሁሉም ሊገባው በሚችል  እና አዝናኝ በሆነ መልኩ በዚሁ መተግበሪያ ይቀርባሉ።መረጃዎችን ለማድረስም ፈጣን መንገድ ነው።በዚህ የተነሳ የብዙዎችን ቀልብ እንዲስብ ሆኗል።ያምሆኖ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ሳይቀር እጅግ እየተዘወተረ  የመጣው የቻይና የተንቀሳቃሽ ምስል ማጋሪያ የራሱ የሆኑ ጥቅምና ጉዳቶች እንዳሉት ናሆም ይገልፃል።
በዚህ የተነሳ ቲክ ቶክ የተለያዩ ሀገራትን ባለሥልጣናት እያወዛገበ ሲሆን፤አጠቃቀሙን ለመገደብ  በዓለም ዙሪያ ያሉ የህግ አውጭዎችም እየተከራከሩ ነው። ባለፈው ሐሙስ የብሪታንያ ባለስልጣናት ለደህንነት ሲባል ቲክ ቶክ በመንግስት የተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ መታገዱን ተናግረዋል።ቀደም ሲልም የአውሮፓ ህብረት ስራ አስፈፃሚ አካል ቲክ ቶክን ከሰራተኞቹ ስልክ ለጊዜው አግዷል።  ዴንማርክ፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጄም፣ኒውዚላንድ፣ ኔዘርላንድ እና ካናዳ በመንግስት በሚተላለፉ ተመሳሳይ ርምጃ መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።

Facebook, Twitter, Instagram, TikTok
ምስል Hideki Yoshihara/AFLO/IMAGO

ባለፈው ወርም ዋይት ሀውስ የዩኤስ የፌደራል ኤጀንሲዎች ቲክቶክን በመንግስት የኤለክትሮኒክ መሳሪያዎች ላይ ለመሰረዝ የ30 ቀናት ጊዜ ገደብ መስጠቱን ተናግሯል።የአሜሪካ ጦር ሃይሎች እና ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የአሜሪካ ግዛቶች መተግበሪያውን በመንግስት መስሪያ ቤቶች አግደውታል።በኒዮርክ ዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ስኮት ጋልወይ መተግበሪያው በባለስልጣናት ዘንድ ስጋት ያዳሳደረበትን ምክንያት ይገልፃሉ።
«አደጋው ቲክ ቶክ በሲሲፒ እና በማንኛውም የቻይና ኩባንያ መካከል ምንም ልዩነት አለመኖሩ ነው። እናም CCP ምዕራባውያንን  የማንቋሸሽ እና የመጣል  የራሱ ፍላጎት አለው»
በመሆኑም በቅርቡ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የቲክቶክ  ኩባንያ  ባይትዳንስ ባለቤቶች መተግበሪያው ላይ ያላቸውን ድርሻ እስካልሸጡ ድረስ ዩናይትድ ስቴትስ ቲክ ቶክን በሀገሪቱ ውስጥ እንደምታግድ ዝታለች። ቲክ ቶክን ለማገድ የሚደረገው ግፊት በአብዛኛው የሚመራው በሪፐብሊካን ህግ አውጭዎች ሲሆን፤ስጋታቸውም ተፈላጊ ይዘቶችን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ  ቤጂንግ ቲክቶክን እንደ  የትሮጃን ፈረስ፣ በመጠቀም የሰዎችን የአሰሳ ታሪክ እና ቦታን በመከታተል  የተጠቃሚዎችን  ውሂብ  ለማግኘት እንዲሁም የተሳሳተ የመረጃ ለማሰራጨት  ልትጠቀም ትችላለች  የሚል ነው። የመረጃ ቴክኖሎጅ ባለሙያው ናሆም ፀጋዬ ስጋቱ መሰረት አለው ይላል።
የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ቲክ ቶክ ላይ እገዳ ሊጣል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፤ ከሳቸው በፊት የነበሩት  ዶናልድ ትራምፕም  በ2020 ዓ/ም ቲክ ቶክን ለማገድ ሞክረው ግን አልተሳካላቸውም።
የቲክ ቶክ ቃል አቀባይ ማውሪን ሻናሃን የሰሞኑን እግድ ተከትሎ እንደተናገሩት  አሜሪካ ብሔራዊ ደህንነትንን መጠበቅ ዓላማዋ ከሆነ  የባለቤትነት ለውጥ ማድረግ በመረጃ ፍሰት ላይ ምንም አይነት አዲስ ነገር አያመጣም ።ችግሩን አይፈታውም ብለዋል።
ከዚህ ይልቅ የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶችን ለመቅረፍ ጠቃሚው መንገድ ግልፅ የሆነ የተጠቃሚ ውሂብ እና ስርዓቶች ጥበቃ የሚያደርግ ጠንካራ የሶስተኛ ወገን ክትትል ማድረግ፣ ማጣራት እና ማረጋገጥ ነው። ብለዋል። ይህንም ኩባንያው አስቀድሞ ሲሰራ መቆየቱን  ተናግረዋል።

Symbolbild | Tiktok und Chinesische Flagge
ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance

ኩባንያው የብሄራዊ ደህንነት ስጋቶችን ለመፍታት ከአሜሪካ ጋር ለሁለት አመታት ያህል ሲሰራ ቆይቷል። ያሉት ሀላፊው ለጠንካራ የመረጃ ደህንነት  ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር (1.4 ቢሊዮን ዩሮ) በላይ ወጪ ማድረጉን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ቲክ ቶክ ለተጠቃሚዎች አዲስ ይዘትን ለማሳየት ስልተ ቀመርን /አልጎሪዝም/ ስለሚጠቀም ወጣቶች ዘንድ ተገቢ ያልሆኑ  ቪዲዮዎች ሊደርሱ ይችላሉ።  የመተግበሪያው ተጠቃሚዎች እርስ በርስ በግል መልዕክት እንዲለዋወጡ የሚያስችል የግንኙነት ገፅታዎች ያሉት በመሆኑም ልጆችን ከማያውቁት ሰው ጋር በማገናኘት ስጋት ላይ ይጥላል።ናሆም እንደሚለው ለልጆች ብቻ የሚያገለግለው«ቲክ ቶክ ኪድስ» የሚባለውም  ቢሆን ከዚህ ችግር የወጣ አይደለም።
በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች እንዳሉት የሚነገርለት ቲክቶክ  በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ውስጥ ታዳጊዎችን ጨምሮ ከ100 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች አሉት ።
በመሆኑም መቀመጫውን በብራስልስ ያደረገው እና ለትርፍ ያልተቋቋመ አክሰስ ኖው የተባለ የዲጂታል መብቶች ድርጅትት  ባልደረባ የሆኑት ኤስቴል ማሴ በዓለም ላይ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለው ቲክ ቶክ  አብዛኛው ተጠቃሚ ወጣቱ ትውልድ በመሆኑ በቻይና መንግስት የሚደረገው ክትትል ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። 

Estelle Massé - Global Data Protection Lead bei der Brüsseler NGO Access Now
ምስል Privat

ነገር ግን መንግስታት ልክ እንደ ቲክቶክ ሁሉ ኢንስታግራምን በመሳሰሉ መሰረታቸው አሜሪካ  የሆኑ  ሌሎች መድረኮች ምን እየሰሩ እንደሆነ መዘንጋት የለባቸውም በማለት አሳስበዋል።
ናሆምም በበኩሉ በሌሎቹ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይመ  ተመሳሳይ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ ይገልፃል።

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ