1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምርጫ ጥሪ በቦሮ ፓርቲ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 25 2015

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሰላም ሰፍኗል ያለው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምርጫ በክልሉ እንዲካሄድ ጥሪ አቀረበ። በክልሉ ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ አለመካሄዱን ፓርቲው ትናንት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/4Lg3X
Äthiopien Logo Boro Democratic Party
ምስል Boro Democratic Party

«ምርጫ ለማካሄድ የሚል የተቀመጠ የጊዜ ዘለዳ የለም»

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ሰላም ሰፍኗል ያለው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምርጫ በክልሉ እንዲካሄድ ጥሪ አቀረበ። በክልሉ ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ አለመካሄዱን ፓርቲው ትናንት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። በዚህ ዓመት በክልሉ ምርጫ ማካሄድ የማይቻል ከሆነ ለሎች ሕገመንግስታዊ አማራጭ መፍትሔዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ፓርቲው አሳስቧል። የፌደራል እና የክልሉ መንግስት ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመቀናጀት ፓርቲው ሕገ ወጥ እና ግጭት ጫሪ አጀንዳ አራማጆች ያላቸውንም እንዲቆጣጠሩ ሲል ጠይቋል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ተራዝሞ መቆየቱንበክልሉ ከሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ዐስታወቀ። የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ተሰማ በአሁኑ ወቅት በክልሉ አብዛኛው ቦታዎች ሰላም በመስፈኑ ምርጫ ባስቸኳይ ተካሂዶ ሕጋዊ መንግሥት በክልሉ መመስረት እንዳለበት ጠቁመዋል። በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ የሚያሰጋ የፀጥታ ችግር አለመኖሩንም ተናግረዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይም በመተከል ዞን ለረጅም ጊዜ የቆየው የሰላም መደፍረስ መረጋጋቱንና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬያቸው መመለስ መጀመራቸውን ፓርቲአቸው እንደሚደግፍ አመልክተዋል። 

Äthiopien | Assosa
ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ አውራጎዳና ላይአውቶቡስ፤ ባጃጆችና ሰዎች ይታያሉምስል Negassa Desalegn

ዞኑ ለተራዘመ ጊዜ ግጭት ውስጥ እንዲቆይ የሚፈልጉ ራሳቸውን «የመተከል አስመላሽ ኮሚቴ» ብለው የሚጠሩ ኃይሎች በግጭት ቀስቃሽ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ኃላፊው ተናግረዋል። በክልሉ ለሦስትና አራት ዓመታት የነበረውን ግጭትና አለመረጋጋት በዘላቂነት ለመቅረፍ የፌደራል እና የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። 

በክልሉ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያ ንቅናቄ (ጉ.ሕ.ዴ.ን) እና የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤ.ሕ.ነ.ን) ታጣቂዎች ጋር የሰላም ስምምነት መደረሱ በክልሉ ሰላም መስፈን አስተዋጽኦ እንዳለውም አቶ ዩሐንስ ተናግረዋል። ነገር ግን የተሐድሶ ስልጠና የወሰዱ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ወደ ክልሉ የፀጥታ ኃይሎች፤ ፍትህ እና ደህንነት መዋቅሮች ውስጥ እንድቀላቀሉ ሊደረግ እንደማይገባ ፓርቲው አሳስቧል።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ለማ በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ የሚል የተቀመጠ የጊዜ ዘለዳ የለም ብለዋል። ከቤኒሻንጉል ጉሙዝና ምርጫ ባልተካሄደባቸው የኦሮሚያ ክልል ውጪ ያሉ ሌሎች ምርጫ ያልተካሄደባቸው የሀገሪቱ ስፍራዎች ምርጫ እንዲካሄድ በቦርዱ ደብዳቤ እንደ ደረሳቸውም ጠቁመዋል።

Grenze zwischen Äthiopien und Sudan
ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የተዘማዘዘ አውራጎዳና ዳር በጋሪ እቃ የያዘ ልጅ ተቀምጦ ከርቀት አንድ ሰውዬ ሲመጡምስል Negassa Dessalegn/DW

በፓርቲው የተጠቀሱትን የሰላም እና ደህንነት ጉዳዩችን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡን ከሚመለከተው የክልሉ ተቋማት መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ባለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 22 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በሰጡት ማብራሪያ በክልሉ ሁሉም ቦታዎች በሚባል ደረጃ ሰላም ሰፍኗል ብለዋል። ድንበር አካባቢዎችና ወረዳዎችን የሚያገናኙ የትራንስፖርት አገልግሎቶችም መጀመራቸውን ኮሚሽነር ሐሩን ዑመር ገልጸዋል። በቤኒሻንል ጉሙዝ ክልል ከአሶሳ ዞን የተወሰኑ ቦታዎች ውጪ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ምርጫ ሳይካሄድ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ