1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሱሉልታ ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጓል

ሰኞ፣ ጥቅምት 6 2010

ባለፈው ሳምንት በኦሮሚያ ክልል ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄደዋል፡፡ ሰልፎቹ በኦሮሞ መብት ተሟጋቾች ዘንድ እምብዛም ድጋፍ አላገኙም፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግስት የክልሉ ነዋሪዎች በሰልፎቹ ላይ ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡ “ሰልፎቹን ማን ጠራቸው?” የሚለው እያነጋገረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ዛሬም በሱልልታ ተመሳሳይ ተቃውሞ ተካሂዷል፡፡

https://p.dw.com/p/2lvrW
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

በሱሉልታ ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጓል

በአዲስ አበባ አቅራቢያ የምትገኘው ሱሉልታ ከተማ ሳምንታዊ የገበያ ቀኗ ሀሙስ ነው፡፡ በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ እና ቅዳሜ ደግሞ አነስ ያሉ ገበያዎችን ታስተናግዳለች፡፡ ዛሬ ቀኑን ሙሉ ግን እንደወትሮው ገበያ አልነበረም፡፡ ሱቆቿ ተዘግተው፣ የታክሲ አገልግሎት ቆሞ በከተማዋ ዋና አውራ ጎዳና ለሰዓታት የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ትንፋሿን ሰብስባ ስትከታተል ነበር፡፡ ሁኔታው ያስፈራቸው ዕለታዊ ክንውናቸውን ትተው፣ በመኖሪያቸው ሁነው ተቃውሞውን ይከታተሉ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሱሉልታ ነዋሪ ዛሬ ረፋዱን በከተማይቱ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ይገልጹታል፡፡ “ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ነበር፡፡ ተቃውሞውን ሰልፉን አይቼ፣ እንዳልጎዳ በማለት ነው የተመለስኩት፡፡ ምን እንደሚሉ አላውቅም ኮኮብ የሌለበት ባንዲራ ይዘው  ነው የወጡት” ይላሉ፡፡

እኚህ ነዋሪ ሰልፈኞቹ ሱቅ ሲያዘጉ መመልከታቸውን እና የታክሲ አገልግሎትም ተቃውሞውን ተከትሎ በከተማይቱ ማቋረጡን  ያስረዳሉ፡፡ ተቃውሞ እንደሚካሄድ ቀድመው የሰሙት ነገር እንዳልነበር የሚናገሩት ነዋሪው በሰልፉ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ የነበራቸውን ጉዞ ሰርዝው፣ ወደቤታቸው ለመመለስ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎችም ሰልፍ እንደሚካሄድ መረጃው እንዳልነበራቸው ገልጸውልናል፡፡  

በጠዋት ወደ ገበያ መውጣታቸውን የሚናገሩ አንዲት የከተማዋ ነዋሪ ተቃውሞው የጀመረው በጋሪ ነጂዎች እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ጋሪ ነጂዎቹ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ወደ ካጂማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሄዱ በኋላ ተማሪዎች እንደተቀሏቀሏቸው ያብራራሉ፡፡ ከዚያ በኋላ የሰልፈኞቹ ቁጥር እያደገ የከተማው ሌላ ነዋሪም አብሯቸው መቃወም እንደቀጠለ ይናገራሉ፡፡ ሰላማዊ ነበር ባሉት በዚህ ተቃውሞ ፖሊሶች ሰልፈኞች ከመጠበቅ ውጭ ምንም ዓይነት እርምጃ አልወሰዱም ይላሉ፡፡ 

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሌላ የከተማዋ ነዋሪም ተመሳሳይ ገለጻ አላቸው፡፡ ሰልፉ ከሶስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ መቆየቱን ይናገራሉ፡፡ እጃቸውን ከጭንቅላታቸው በላይ በማጣመር ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የነበሩ ሰልፈኞች ያሰሟቸው የነበሩትን መፈክሮች ይዘረዝራሉ፡፡ “በመንግስት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ነው በአብዛኛው ያሰሙት፡፡ ‘አገዛዙ በቃን፣ የታሰሩት ይፈቱልን፣ ነጻነታችን ይከበርልን’ አይነት ነው የተላለፈው መልዕክት፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የብሩን በመጠን ባላውቅም ብዙ ብር እርዳታ ተሰብስቧል፡፡ በሰላም ተጠናቋል ሰላማዊ ሰልፉ፡፡ የኦሮሚያ ፖሊሶች እየጠበቁ ነው የተጠናቀቀው” ብለዋል ነዋሪው፡፡

Äthiopien Oromiya MBO Universität
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

በሰልፉ ላይ ለኦሮሚያ ክልል አስተዳደር እና ለክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ድጋፎች ሲደመጡ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን አልረዳም በሚልም የፌደራል መንግስት ላይ ወቀሳ መሰንዘሩን ጠቁመዋል፡፡ በሰልፉ ላይ ድጋፍ እና ተቃውሞ ቢስተናገድም ሰልፉን ማን እንደጠራው እንደማይታወቅ ይናገራሉ፡፡ “እንደውም ከትላንት ጀምሮ አትውጡ፣ ማንም አልጠራችሁም እየተባለ ነው የወጡት፡፡ የጠራው አካልም አይታወቅም፡፡ በተወሰኑ ልጆች ነው የተጀመረው፡፡ ከዚያ በኋላ ትላልቆቹ መጥተው ተቀላቀሉ፡፡ ለተወሰነ ሰዓት ዝግ ነበር፡፡ ብዙ ሰው ነው የወጣው” ይላሉ የሰልፉን ተሳታፊ ብዛት ሲያስረዱ፡፡

ሱልልታ ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ መመለሷን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በኦሮሚያ አሁን በተከታታይ እየተካሄዱ ላሉ ተቃውሞች መነሻ በነበረችው አምቦም ባለፈው ረቡዕ የሆነው ተመሳሳዩ ነበር፡፡ በሰላም የተጠናቀቀው ይህ ሰልፍ “ዱብ እዳ እንደነበር” ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ አንድ የአምቦ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል፡፡ እንደ አምቦ ሁሉ በዚያው ቀን ጥቅምት 1  ቀን 2010 ዓ.ም ሻሸመኔ እና ዶዶላ ላይም ሰላማዊ ሰልፎች ተደርገዋል፡፡ በሻሸመኔ የነበረው ሁኔታ ግን እንዲህ አይነት ሰላማዊ ሰልፎች ሲካሄዱ ትልቅ ሚና የነበራቸውን በውጭ ሀገር የሚኖሩ የኦሮሞ መብት ተሟጋቾች ጭምር ግር ያሰኘ ነበር፡፡ 

ለእንዲህ አይነት ሰልፎች ድጋፍ በመስጠት የሚታወቁ መቀመጫቸውን በውጭ ሀገር ያደረጉ ተሟጋቾች እየተካሄዱ ያሉ ሰልፎችን ድጋፍ ነፍገዋል፡፡ ወጣቶችም እንዳይሳተፉ ይመክሩ ይዘዋል፡፡ በኖርዌይ የሚኖረው ግርማ ጉተማ ከኦሮሞ መብት ተከራካሪዎች አንዱ ነው፡፡ ቀደም ሲል ይካሄዱ የነበሩትን ሰልፎች ከአሁኖቹ ጋር ያነጻጽራል፡፡ 

“እነዚህ ሰልፎች እንደድሮው የተቀናጁ አይደሉም፡፡ በፊት ምንድነው? ቀደም ብለን ነገሮችን ግልጽ አድርገን ነው ስንንቀሳቀስ የነበረው፡፡ የአሁኖቹ ግን የተቀናጁ አይደሉም ሁለተኛ ደግሞ ሻሸመኔ ላይ የተከሰተው አሁን በጣም አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ በአጠቃላይ ብዙ ሰዎች ናቸው የሞቱት፡፡ ሻሸመኔ ላይ ሰልፈኛውን እየመሩ ወደ ወታደር ካምፕ ላይ የሚወስዱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ያንን ከሰማን፣ ካጣራን በኋላ ነው በነገርህ ላይ እንዲህ እንደድሮው ለመብት ጥየቃ እንዳልሆነ እና የሆነ አካል እንደጠለፈው ዓይነት መረጃ የደረሰን፡፡ እና የእኛን ቄሮዎች በፊት ሪፖርት የሚያደርጉልንን፣ የተወሰኑትን ጠልፈውብን ነበር፡፡ አሁን የእኛዎቹ ከዚያ ውስጥ ወጥተዋል፡፡  

የድሮው እንግዲህ ግልጽ የሆነ መናበብ አለ፡፡ እኛ የአድቮኬሲ፣ የመገናኛ ብዙሃን ስራ ነው የምንሰራላቸው፡፡ ሰዎቹ መረጃ ይሰጡናል ማለት ነው ከዚያ በግልጽ በመላው ኦሮሚያ ይካሄዳል ተብሎ  ነበር የምንጀምር የነበረው፡፡ ይሄኛው እኮ ከበፊቱ ጋር በፍጹም አይገናኛም፡፡ መናበብም አልነበረም፡፡ ውስጥ ለውስጥ ‘ይሄን ጽሁፍ ለ100 ሰው ላክ፣ ነገ ስብሰባ ይኖራል’ የሚል ነገር ከመጀመሪያው የሰልፍ ቀን ሁለት፣ ሶሰት ቀናት ቀደም ብሎ እንደዚያ ሲያሰራጩ ነበር፡፡ እኛም ምላሽ አልሰጠንም፡፡ ዝም ብሎ ነገር መስሎን፡፡ ስናየው ነገሩ ጥሩ እንዳልሆነ እና ወጣቱ ከእንደዚህ አይነት ነገር እንዲቆጠብ [ነግረናል]፡፡ ሰልፍም ካስፈለገ በስርዓት፣ ተቀናጅቶ፣ ሰላማዊ ሆኖ፣ ውጤት ያለው እና ግልጽ የሆነ ጥያቄ የያዘ ሰልፍ እናደርጋለን እንጂ ዝም ብሎ አሁን የፖለቲካዊ ሁኔታው ስለሞቀ ብቻ እየተወጣ ሰው አላስፈላጊ መስዋዕትነት መከፈል የለበትም በሚል አቋም ነው የታቀብነው” ይላል ግርማ ስለተሟጋቾቹ ድጋፍ መንሳት ሲናገር፡፡      

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን የኦሮሚያ መንግስት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ