1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ከ20 በላይ ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ረቡዕ፣ መጋቢት 1 2013

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን ታጣቂዎች ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። የአይን እማኞች እንደሚሉት በዞኑ ደቢስ በተባለ ቦታ ጥቃቱ የተፈጸመው ባለፈው እሁድ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ቤተ-ክርስቲያን ባመሩበት ወቅት ነው።

https://p.dw.com/p/3qRI1
Karte Äthiopien Ethnien EN

በሆሮ ጉዱሩ ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ተገደሉ

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ከባለፈው እሁድ ጀምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ጥቃቶች መድረሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። አበደንጎሮ በተባለ ወረዳ ከ20 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉንና በርካታ ሰዎች ደግሞ መታገታቸውንም ነዋሪዎቹ አክለዋል። ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ደቢስ በተባለ ቦታ ከሞቱት መካከል ህጸናትና ሽማግለዎችም ይገኙበታል። ብዙ ቁጥር ያላቸው የጸጥታ ሀይሎችም በስፍራው መድረሳቸውን አክለዋል። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን  በታጣቂዎች ደረሰ የተባለውን ጥቃት አስመልክቶ  ከዞኑ አስተዳዳሪ ተወካይና ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ማብራሪያ ለመጠየቅ በስልክ ያደረኩት ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸው አልተሳካም።

በዞኑ አቤደንጎሮ ወረዳ ነዋሪ መሆናቸውን የነገሩን አቶ ዩሱፍ ደቢስ በተባለች ቦታ የበርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉንና ሌሎች መታገታቸውን ገልጸዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው አብዛኞው ሰው ወደ ቤተክርሲቲያን ሄደው በነበረበት ሰዓት ሲሆን ጥቃት አድራሾቹም ሌሎች 20 የሚደርሱ ሰዎችን ማገታቸውን አክልዋል። በተለያዩ ቀበሌዎች ውስጥ የጸጥታ ሀይሎች ለስራ ወደ ሌላ ስፋራ መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ ታጣቂዎችም ወደ መንደር በመመግባት ጥቃት ስለ ማድራሳቸው አብራርተዋል።  

ሌላ የሆሮ ጉድሩ ዞን  ነዋሪ በነገሩን መረጃ መሰረት ደግሞ የጸጥታ ሀይሎች እና ሚሊሻዎች በአካባቢው ሽፍቶች አሉ በማለት አሰሳ በማድረግ ላይ እንደነበር የገለጹ ሲሆን በተለያዩ አቅጣጫ ከተንቀሳቀሱ የጸጥታ ሀይሎች መካከል አንዱ ህይወቱ ማለፉን ተናግረዋል። በወረዳው በደረሰው ጥቃትም በርካታ ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን  የጠፉ ሰዎችም እየተፈለጉ እደሆነ ነዋሪው ገልጸዋል። 

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ተፈጠረ በተባለው ጥቃትና የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ እና ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት ፍቃደኛ ባለመሆናቸውና ሌሎችም  ስልክ ባለማንሳታቸው  ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም። 
ከወራት በፊትም በሆሮ ጉድሩ ወለጋ አሙሩ ወረዳ በደረሰው ጥቃት እንዲሁ የሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ የመንግስት ገልጾ ነበር።በአካባቢው በደረሰው ጥቃትም እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጋቸውን በወቅቱ ተገልፆ ነበር። 

ነጋሳ ደሳለኝ
አዜብ ታደሰ